“ችግሩን ለመቅረፍ ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ በተዘዋዋሪ ፈንድ ተመድቦላቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ ነው፡፡” በአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የሸማቾች ቡድን ዳይሬክቶሬት
የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ገበያን ማረጋጋት አንዱ ኃላፊነታቸው ነው፡፡ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ 813/2006 የሸማቹ መብት የሚከበርበትን ሁኔታ ያስቀምጣል፡፡ ሆኖም በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ሐሳባቸውን እንዲያጋሩን የጠየቅናቸው ሰዎች እንዳሉት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ጠንክረው እንዲወጡ እና የኑሮ ውድነቱን ሊቋቋሙ የሚችሉበት አደረጃጀት የላቸውም፤ ጠንካራ ማኅበራት እንዲሆኑም አባሉ ግፊት እያደረገ አይደለም፤ የቁጠባ አሰራራቸውም ደካማ ነው፤ በዚህም ምክንያት የመሠረታዊ ፍጆታ እቃዎች የዋጋ ግሽበት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ነው፡፡ ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ጠንካራ የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት እንዲኖሩ አባላቱ ‹‹ምርት መጥቷል ውሰዱ›› ሲባሉ ሄደው የሚወስዱ ብቻ ሳይሆኑ በየጊዜው ማኅበራቸው በተመጣኝ ዋጋ ምርት እንዲያቀርብ የሚጠይቁ መሆን አለባቸው፡፡
በባሕር ዳር የሽምብጥ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር ሥራ አስኪያጅ እንዳላማው አቤ በወቅቱ ምርት ከሌላ አካባቢ በማምጣት መጋዘን ላይ አስቀምጠው በችግር ጊዜ ለሸማቾች ለማከፋፈል የገንዘብ (ካፒታል) ችግር እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ ለመከዘንም የቦታ ችግር እንዳለ የሚናገሩት ሥራ አስኪያጁ በባሕር ዳር ከተማ 11 የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት እንዳሉና አብዛኞቹ የመስሪያና መሸጫ ቦታ እና የገንዘብ ችግር እንዳለባቸው እንደሚያውቁ ተናግረዋል፡፡
‹‹በዚህም ምክንያት ሸማቹን በሚያረካ መልኩ እያገለገሉ አይደሉም፤ በማኅበረሰቡ ተነሳሽነትና ፈቃድ በመቋቋማቸው አባል ሲሆኑ በሚከፍሉት ክፍያና ማኅበሩ እየሠራ ከሚያካብተው ንብረት ውጭ በሰፊው የማኅበር አባሉን ፍላጎት ማርካት የሚያስችል የገንዘብ አቅም የለውም›› ብለዋል፡፡ ይህም ወደ አርሶ አደሩ ወርዶ ምረት ለመሰብሰብና የኑሮ ውድነቱን ሊቀርፍ በሚችል መልኩ ላለመንቀሳቀሳቸው ምክንያት መሆኑን ነግረውናል፡፡ መንግሥት ለሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ትኩረት እንዳልሰጠ ያመለከቱት ሥራ አስኪያጁ ትኩረት መነፈጉ ኅብረተሰቡ የሚፈልገውን ምርት እንዳያገኝ እንዳደረገው አስታውቀዋል፡፡ ‹‹መንግሥት ትኩረት ቢሰጠው ኖሮ አሠራሩም ዘምኖ መዋቅሩም ይስተካከላል ነበር፤ ኑሮ ሲወደድ ብቻ ሸማቾች የትገቡ ተብለን እንፈለጋለን›› ሲሉ ሥራ አስኪያጁ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
በአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የሸማቾች ቡድን ዳይሬክቶሬት የትምህርትና ስልጠና ባለሙያ አቶ ደመላሽ ታደለ የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በሰፊው ገብተው የገበያ ማረጋጋት ሥራ አለመሥራታቸውን ማረጋገጣቸውን አመልክተዋል፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ በ2012 በጀት ዓመት ከ65 ሚሊዮን 481 ሺህ ብር በላይ በተዘዋዋሪ ፈንድ ተመድቦላቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑንና ሁሉም ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ቦታ ተሰጥቷቸውና የምረት ማከማቻ መጋዘን ኖሯቸው እንዲሸጡ እየተደረገ እንደሆነ አስታውቀዋ፡፡
የሌሎች የክልሉ አካባቢዎችም ጥሩ ተሞክሮ እንዲቀመር ለሌሎች ማኅበራት ማሳወቃቸውንም ገልጸዋል፤ ‹‹ለአብነት ባለፍነው ዓመት ሰቆጣ ከተማ የሚገኘው ማኅበር ምርት በሚደርስበት ወቅት ከጎንደርና ጎጃም ምርታማ አካባቢዎች የሰብል ምርት ገዝቶ በቅናሽ ዋጋ መሸጥ ችሏል፤ ይህም ሌሎች ሊማሩበት የሚገባ ነው›› ብለዋል፡፡
የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ምርቱን በወቅቱ ገዝተው ለተጠቃሚው ከማቅረብ ይልቅ ከነጋዴ ዋጋ ልዩነት በሌለው ሁኔታ እንደሚያቀረቡም ተናግረዋል፡፡ በምርት ወቅት መሸመት ዋነኛ ጠቀሜታው እንደ በቆሎና ጤፍ ያሉ የሰብል ዓይነቶች የዋጋ ቅናሽ ስለሚኖራቸው ገዝቶ መከዘን እና በሚወደድበት ጊዜ በቅናሽ መሸጥ ለችግሩ ሁነኛ መፍትሔ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በማኅበራቱ የነበሩት የመዋቅርና የሰው ኃይል ችግሮች እንዲፈታላቸው እየተደረገ እንደሆነ የተናገሩት ባለሙያው ነገር ግን አንዳንዶች መሠረታዊ ከሆኑት ምርቶች ውስጥ ስኳርና ዘይት ብቻ ከማሠራጨት ወጥተው ሥራውን እንዲያሰፉ መክረዋል፡፡
‹‹የኢንዱስትሪ ምርቶችን መሸጥ አለባቸው፤ ሸማቹን በሚያረካ ደረጃ ላይ መገኘት ይጠበቅባቸዋል፤ በመንግሥት በኩልም ለጉዳዩ ትኩረት ስጥቶ የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተጠናክረው ሸማቾች በቀጥታ እንዲገበያዩ መድረግ አለበት፤ አርሶ አደሩም የሚሸጥበት የራሱ ቦታ በሰፊው ማዘጋጀት ይጠበቃል፤ የተጀመሩ አሰራሮች ተጀምረው የሚቀሩ ሳይሆን ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማድረግ ይገባል›› ብለዋል፡፡
ንግድ በውድድር እንዲመሠረት፣ የሸማቾች መብትና ጥቅም እንዲከበር የገበያ ማረጋጋት ላይ የሚሠራው በኢፌዴሪ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ኅብረተሰቡ በመደበኛ ገበያ በኩል ምርቶችንና ዋጋቸውን እንዲረዳ ለማድረግ የማስተዋወቅ ሥራ መጀመሩንም አመልክተዋል፡፡
የኢፌዴሪ ንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን የግንዛቤ ማሳደግና ሕግ ተፈፃሚነት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ መሰለች ወዳጆ እንዳሉት ለክልሎች ስልጠና በመስጠት ስለክንውኖች በየስድስት ወሩ ምክክር እየተደረገ ነው፡፡ ‹‹መንግሥት በድጎማ በሚያቀርባቸው የመሠረታዊ ፍጆታ ምርቶች ላይ አላግባብ ዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ቁጥጥር እናደርጋለን›› ያሉት ወይዘሮ መሰለች ገበያው እንዴት እየሄደ ነው የሚለው በባለስልጣኑ በሳምንት ሦስት ጊዜ እንደሚዳሰስ ተናግረዋል፡፡ የሳምንቱ ደግሞ ካለፈው ሳምንትና ጊዜያት ጋር በማነፃፀር ትንታኔ እየተሠራ ነው፡፡ ‹‹ሆኖም የገበያው ዋጋ እንዲወርድ ተደርጎ ኅብረተሰቡ እፎይ የሚልበት ሁኔታ አልተፈጠረም፤ ብዙ የሚጠበቅ ሥራ አለ፤ በዚህ ጊዜ ገበያው የበለጠ እንዳይንር ለማርገብ ጥረት እየተደረገ ነው፤ የምርት ወደ ገበያ በደንብ ማስገባት ይጠበቃል›› ብለዋል፡፡ ኅብረተሰቡም አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ሲያጋጥመው ለባለስልጣኑ ጥቆማ በመስጠት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ወይዘሮ መሰለች ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ