
ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በዛሬው እለት አዲሱን የዓባይ ወንዝ ድልድይ ግንባታ ሂደትን ተመልክተዋል።
በመረሐ ግብሩ ላይ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማእረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን፣ የርእሰ መስተዳድሩ ልዩ አማካሪ አቶ ደሳለኝ አስራደ እና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በጀት እየተገነባ የሚገኘው አዲሱ የዓባይ ወንዝ ድልድይ ግንባታ የማጠናቀቂያ ሥራዎች እየተፋጠኑ ይገኛል። ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በነባሩ የዓባይ ወንዝ ድልድይ ላይ የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ መቅረፉ የሚያስችል ነው።
የድልድዩ ግንባታ ተቋራጭ የቻይናው ኮሙዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ ሲሆን ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየሠራ መሆኑን ገልጿል።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ የድልድዩ ግንባታ ሒደት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ከርእሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ርእሰ መሥተዳድሩ እንደገለፁት ድህነትን ማጥፋትና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ የሚቻለው በቅድሚያ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ተደራሽ ማድረግ ስንችል ነው ብለዋል።
ድልድዩ የሕዝባችንን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች ለመቅረፍ ጉልህ ድርሻ አለው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ፤ ግንባታውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ልዩ ትኩረት ተሰጥተው እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
አዲሱ የዓባይ ወንዝ ድልድይ የፊታችን ሰኔ ወር መጨረሻ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሎም ይጠበቃል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!