“የእጣንና ሙጫ አምራቾች በዘመናዊ መንገድ እያለሙ እንዲጠብቁና ውል እንዲወስዱ አድርገናል” የአማራ ክልል አካባቢና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን

166

ባሕር ዳር: ግንቦት 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) እጣንና ሙጫ በአማራ ክልል ከሚመረቱ ገበያ ተኮር ምርቶች በገቢ ደረጃ ግንባር ቀደም  ቦታ  እንደሚይዝ  የአማራ ክልል አካባቢና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የደን ባለሙያ መንግሥቱ አገኘሁ ነግረውናል።

ባለሙያው እንዳሉት ከአንድ ዛፍ በዓመት እስከ 30 ኩንታል የእጣን ምርት  ይገኛል። የአንዱ ኩንታል እጣን በባለፈው ዓመት ዋጋ ሲሰላ 23 ሺህ ብር  ተሽጧል፡፡ የእጣን ምርቱ ተበጥሮ ለገበያ ቢቀርብ ደግሞ የተሻለ ዋጋ እንደሚያወጣ ያስረዳሉ፡፡ ከእጣን እና ሙጫ የሚገኘው ገቢ በአካባቢው ከሚመረተው የሰሊጥ፣  ጥጥና ማሾ ከሚገኘው ገቢ በ10 እጥፍ እንደሚበልጥም ነው የተገለጸው፡፡

ታዲያ ይህን ከፍተኛ ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታ ያለውን ሃብት ከማልማትና ለወጣቶችም የሥራ እድል መፍጠሪያ ዘርፍ አድርጎ በመሥራት በኩል ችግሮች እንደነበሩ ነው ባለሙያው ያነሱት።  በተለይም ደግሞ ሃብቱ በብዛት የሚገኘው በክልሉ ሞቃታማ  አካባቢ  በመኾኑ የአካባቢውን የአየር ንብረት ተቋቁሞ የማምረት ችግር በወጣቱ በኩል እንደነበረ  አንስተዋል።

እየተመናመነ የመጣውን ሃብት ጠብቆ ለማልማት በ2010 ዓ.ም በክልል ደረጃ መመሪያ ወጥቷል።  በዚህም  ወጣቶችን በማደራጀትና ለአምራች ባለሃብቶች እና ድርጅቶች  በየዓመቱ  ውል በመሥጠት  የማምረት ሥራ  እንዲሠሩ  ተደርጓል። በዚህ ዓመት ብቻ  60  የሚኾኑ ነባር እና አዲስ እጣንና ሙጫ አምራች ማኅበራትና ድርጅቶች  ፈቃድ ወስደው በማምረት ላይ ናቸው።

ለአምራቾች ሃብቱን ማምረት ብቻ ሳይኾን እንዴት መጠበቅ እንዳለባቸው ውል እንዲወስዱ ተደርጓል።  ሃብቱን በዘመናዊ መንገድ እንዲያመርቱ በየዓመቱ ሥልጠና እየተሰጠም ነው። ማኅበረሰቡ  የሀብቱን ጠቀሜታ ይበልጥ ተረድቶ ወደ ምርት እንዲገባ ለማድረግ ተቋሙ የዳሰሳ ጥናት እያደረገ ይገኛልም ነው ያሉት።

ለመኾኑ የእጣንና ሙጫ ምርቱ ለምን አገልግሎት ይውላል?

የእጣን ምርቱ በውጭ ሀገራት ተፈላጊ  እንደኾነ ባለሙያው ገልጸዋል። የእጣን ምርቱ ደረጃ ያለው ሲኾን ከአንደኛ እስከ አራተኛ ደረጃ ያለውን ምርት ወደ  ጣሊያን፣  ታይላንድ፣ ቻይና፣ ዱባይ፣ ፈረንሳይና የመሳሰሉ ሀገራት  እንደሚላክም ነው ያስገነዘቡት።  ምርቱ ለሽቶ፣ ለውስኪና የመሳሰሉ አልኮል መጠጦች፣  ለብስኩት ፋብሪካዎችና መሰል ዘርፎች ጥቅም ላይም ይውላል። ሃብቱን በክልሉ እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

የሃብቱን ሽፋን እንዴት ማሳደግ ይቻላል?

ዘሩን በችግኝ ጣብያ አፍልቶ  በመትከል፣ ሃብቱ ያለበትን አካባቢ ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ በመከለል ዘሩ እንዲበቅል በማድረግ፣ ከቅርንጫፉ ወይንም ከግንዱ ቆርጦ ከሌሎች ጋር በማዳቀል ሃብቱን  የማራባት  ሥራ  መሥራት ይቻላል።  ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ በመከለል በራሱ እንዲበቅል ወይም ራሱን እንዲተካ  ማድረግ ሃብቱን በዘላቂነት ለማስጠበቅ ተመራጩ መንገድ እንደኾነ ገልጸዋል። ግንዱን ቆርጦ በመትከል የማስፋት ሥራ ደግሞ ሁለተኛው አማራጭ ተደርጎ ይወሰዳል።

ክልሉም ሃብቱን ለመጠበቅ አምራቾች በዘመናዊ መንገድ እያለሙ እንዲጠብቁና  ውል እንዲወስዱ ማድረጉን ነው የገለጹት።

በአማራ ክልል፦

👉 ከ363 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በእጣንና ሙጫ  ደን የተሸፈነ ነው።

👉 የምዕራብ ጎንደርና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ደግሞ ሰፊውን የደን ሽፋን ይይዛሉ።

👉 በ2014 ዓ.ም ከ3 ሺህ 800 በላይ ኩንታል እጣን  ተመርቷል። አንድ ኩንታል  እጣን ምርት ደግሞ እስከ 23 ሺህ ብር ተሽጧል።

ዘጋቢ፦  ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleባለፉት 10 ወራት 1 ሺህ 140 ኪሎ ሜትር መንገድ ጠግኖ ለአገልግሎት ማብቃቱን በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የኮምቦልቻ ቅርንጫፍ ገለጸ።
Next articleአቶ ደመቀ መኮንን በቤላሩስ የኢትዮጵያ የክብር ቆንስል ከሆኑት ሚስተር ዲሚትሪ ሉካሼንኮ ጋር ተወያዩ።