
ባሕር ዳር ፡ ግንቦት 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአገልግሎት ብዛት የተበላሸ 1ሺህ 140 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድና በጦርነት ጉዳት የደረሰበትን አንድ ድልድይ መልሶ በመጠገን ለአገልግሎት ማብቃቱን በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የኮምቦልቻ ቅርንጫፍ አስታወቀ፡፡
በቅርንጫፉ የመንገድ ኔትዎርክና ደህንነት ማኔጅመንት ዳይሬክተር ኢንጂነር ቃልኪዳን ተሾመ ለኢዜአ እንደገለጹት በብልሽት ምክንያት ለትራንስፖርት አስቸጋሪ የሆነ መንገድና ድልድይ መልሶ በመገንባት ለአገልግሎት የማብቃት ሥራ እየተሰራ ይገኛል።
በተያዘው በጀት ዓመትም ከአገልግሎት መብዛት ተበላሽቶ የነበረ 1ሺህ 627 ኪሎ ሜትር መንገድ በ515 ሚሊዮን ብር ለመጠገን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት አስር ወራት በተደረገ እንቅስቃሴም 1ሺህ 140 ኪሎ ሜትር መንገድ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ተጠግኖ ለአገልግሎት መብቃቱን ነው የገለጹት።
ዳይሬክተሯ እንዳሉት ጥገና ከተደረገላችው መንገዶች መካከል ኮምቦልቻ-መካነ ሰላም፣ ደሴ-ከሚሴ፣ ደሴ-ኩታበር-ተንታ፣ ወልድያ- ፍላቂት፣ ቆቦ-ላል ይበላ፣ አፋር ሂዳ-ያሎና ሌሎችም ይገኙበታል።
በተጨማሪም ከአዲስ አበባ-ደሴ-ቆቦ-መቀሌ በሚወስደው መንገድ ተሰብሮ የነበረው “አልውኃ” ድልድይ በ42 ሚሊዮን ብር ተጠግኖ ለአገልግሎት እንዲበቃ መደረጉን አስታውሰዋል።
ድልድዩን ጨምሮ ለተከናወኑ ከባድ፣ ድንገተኛና መደበኛ ጥገናዎች ከ339 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉንም ኢንጂነር ቃልኪዳን አስታውቀዋል።
በቀሪ ወራትም ቅድሚያ የሚሰጣቸውን መንገዶች ጠግኖ ለመጨረስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።
መንገዱ ተጠግኖ ለአገልግሎት መብቃቱ በኅብረተሰቡ ላይ ይደርስ የነበረውን እንግልት ከማስቀረት በላይ የተሽከርካሪን ጉዳት እንደሚያስቀርም ተገልጿል።
ባለፈው ዓመት 315 ኪ.ሜ መንገድ በ156 ሚሊዮን ብር ወጪ ተጠግኖ ለአገልግሎት ማብቃት እንደተቻለም ተመላክቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!