የጣና ሐይቅ የዓሣ ምርት እንዲጨምር ሕገደንቦችን መተግበር እንደሚገባ የአማራ ክልል እንሥሣትና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት አሳሰበ፡፡

57

ደብረ ታቦር፡ ግንቦት 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከ35 እስከ 40 ሺህ ቶን እምቅ የዓሣ ምርት ውስጥ 20 ሺህ ቶን የሚኾነው ከጣና ሐይቅ እንደሚገኝ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ ይሁንና ጣና ሐይቅ የስፋቱን ያክል ከፍተኛ የዓሣ ምርት እንዳይሰጥ በርካታ ችግሮች አጋጥመውታል፡፡ ከችግሮቹ መካከልም ሕገ ወጥ የዓሣ ማስገር አንዱ ነው፡፡

ይህንን ከዘርፉ ላይ ሊገኝ የሚገባውን የዓሣ ምርትና ጥቅም የሚያመክን ተግባርን ለመከላከል የአማራ ክልል እንሥሣትና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት በጣና ዙሪያ ከሚገኙ ወረዳዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

የፎገራ ወረዳ እንሥሣትና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዋለልኝ አሻግሬ ፈቃድ ሳይዙ ማስገር፣ ባልተፈቀዱ ቁሳቁሶች ማስገር እንደሚስተዋል ተናግረዋል፡፡

የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ተወካይ አስተዳዳሪ አየለ እንግዳው በወረዳቸው ችግሩን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሕገ ወጥ ዓሣ ማስገር ሥራን ለመከላከል የባለ ድርሻ አካላት ቅንጅት ውስንነት በተለይም የፍትሕና የጸጥታ አካላት ትብብር አነስተኛነት ጉልህ ችግር መኾኑን የተናገሩት ደግሞ የደራ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አዳነ ካሣ  ናቸው፡፡

የምሥራቅ ደንቢያ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኢንስፔክተር ዋኘው አታለል፤ ወቅታዊ የሕግ የበላይነት አለማከበርና ለዘርፉ ትኩረት አለመሰጠቱ ችግሩን እንዳባባሰው ገልጸው ለኅብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ መፍጠር ችግሩን እንደሚቀንሰው አስረድተዋል፡፡ በቀጣይም ተቋማቸው ጠንክሮ በመሥራት ኀላፊነቱን እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል እንሥሣትና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ነጋ ይስማው የችግሮቹ መንስኤዎች የኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማነስ፣ በመንግሥት በኩል የትኩረት ማነስና ተቀናጅቶ አለመሥራት መኾናቸውን ተናግረው  መፍትሄውም በውይይት ግንዛቤ መያዝና ሕጉን መተግበር መኾኑን አስገንዝበዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ከጣና ሐይቅ የሚያገኘው ከፍተኛ የዓሣ ምርት እንዲቀጥል በባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር እንዲተገብርና ሕገወጥ ዓሣ ማስገርን እንዲያቆምና እንዲከላከልም  አቶ ነጋ ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየካንሰር በሽታን መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችል የምርምርና የካንሰር መረጃዎች መዛግብት ጥምረት ይፋ ኾነ።
Next article“የማዕድን ሃብታችንን በአግባቡ በማልማት የሀገራችንን ኢኮኖሚ እንገነባለን” የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ