የካንሰር በሽታን መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችል የምርምርና የካንሰር መረጃዎች መዛግብት ጥምረት ይፋ ኾነ።

41

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት የአፍሪካ ሀገራትን ያካተተ የካንሰር በሽታን መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችል የምርምርና የካንሰር መረጃዎች መዛግብት ጥምረት ይፋ ተደርጓል።

ኢትዮጵያ ጥምረቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ አማካኝነት እንደምትመራው ተገልጿል።

የአፍሪካ ካንሰር መረጃዎች መዛግብት ዓመታዊ ስብሰባ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

የአፍሪካ ካንሰር መረጃዎች መዛግብት ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ጥምረት የተመሰረተና 25 አባል ሀገራት የተካተቱበት በጥቅሉ 35 የመረጃ መዛግብት የያዘ ጥምረት ነዉ፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ  ካንሰር ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት በዓመት ወደ 533 ሺህ የሚገመቱ ሰዎች እንደሚሞቱና በኢትዮጵያ በየዓመቱ ወደ 77 ሺህ የሚጠጉ አዳዲስ ሰዎች  የካንሰር ሕመምተኛ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

በተለይ ደግሞ ሴቶች የጡትና የማህፀን በር ካንሰር ሰለባ በማድረግ ለስቃይ እንደሚዳርግና የማኅበረሰብ ቀውስ እንደሚያመጣ ለአብነት አንስተዋል።

በዚህ ረገድም ጥምረቱ በዋናነት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት በሴቶች ላይ የሚከሰተውንና በርካቶችን ለሕመምና ለሞት የሚዳርገውን የጡትና የማህፀን በር ካንሰር በሽታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

ጥምረቱ ላደረገው ጥናት ምስጋናቸውን አቅርበው የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

መንግስት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የካንሰር ክትትልን ውጤታማ ለማድረግ በጥምረቱ አማካኝነት ተግዳሮቶችን ለመለየትና ለመቅረፍ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ለፕሮጀክቱ ስኬትም አስተዋፅኦ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል ሚኒስትሯ።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጡት ዶክተር አንዷለም ደነቀ በበኩላቸው የካንሰር በሽታን መከላከል እና መቆጣጠር ቅንጅታዊ ሥራን እንደሚጠይቅና ለዚህም ዩኒቨርስቲ የጥምረቱ መመስረት  የአፍሪካ አገራት የካንሰር የምርምር አቅምን እንደሚያሳድግ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ በመጀመሪያ ደረጃ የጤና ተቋማት የሴቶችን ካንሰር ለመቆጣጠር እንደሚረዳ አመልክተዋል።

ዶክተር አንዷለም ጥናቱ የካንሰር ምርምር አቅምን የሚያሳድግ እንዲሁም በመረጃ ጥንቅርና  በምርምር ድጋፍ በማድረግ የካንሰር በሽታን ለመከላከል ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት መካከል ያለውን የመረጃ ልውውጥ የተሻለ ያደርገዋል ነው ያሉት።

በጥናትና ምርምሩ ላይ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ምሁራንና የጤና ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል።

ትላንት የተመሰረተው ጥምረት በጀርመን መንግስት እንደሚደገፍ የጤና ሚኒስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ያሰፈረው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአቶ ደመቀ መኮንን ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ ጋር ተወያዩ።
Next articleየጣና ሐይቅ የዓሣ ምርት እንዲጨምር ሕገደንቦችን መተግበር እንደሚገባ የአማራ ክልል እንሥሣትና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት አሳሰበ፡፡