
ባሕር ዳር: ግንቦት 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር የሚገኙ ወረዳዎች መንግሥት እያከናወነ ያለውን የሕግ ማስከበር ተግባር እንደሚደግፉ አደባባይ በመውጣት ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ የደቡብ ጎንደር ዞን ወረዳዎች በተከናወነው የአደባባይ ላይ ድጋፍ መንግሥት ሕግን በማስከበር ሕዝቡ የሰጠውን ዝቅተኛ ኀላፊነት እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡
የአደባባይ ላይ ድጋፉን አስመልክተው ለአሚኮ ማብራሪያ የሰጡት የደቡብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጥላሁን ደጀኔ ሕዝቡ መንግሥት እያከናወነ ያለው ተግባር ሕግ የማሰከበር እንደኾነ እንደሚገነዘቡ ማረጋገጡን ነው ያስረዱት፡፡
አቶ ጥላሁን ደጀኔ የአደባባይ ላይ ድጋፉ ዋና ዓላማ ጽንፈኝነትን ለመዋጋት መንግሥት እያካሄደ ያለውን ዘመቻ ሕዝቡ ምን ያክል እንደሚደግፈው ማሳየት እንደኾነም አስረድተዋል፡፡
የሀገር መከላከያ ጽንፈኝነትን ለማጥራት እየወሰደ ባለው ሕግን የማስከበር ዘመቻም ሕዝቡ ድጋፍ እንደሚሰጥ እና እየሰጠም እንደሚገኝ ባካሄደው የአደባባይ ድጋፍ ማረጋገጥ እንደተቻለም አብራርተዋል፡፡
ሕዝቡ ባካሄደው ሰልፍ ሕግ ሲጣስ ንጹሐን ላይ ግድያ እንደሚፈጸም መግለጻቸውን የተናገሩት አቶ ጥላሁን ይህን ሕገወጥ ተግባር ከወዲሁ ማስቆም እንደሚገባ በሰልፉ መልእክት ተላልፏል፡፡
ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!