
ባሕር ዳር ፡ ግንቦት 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የድምጻዊት ሂሩት በቀለ የቀብር ሥነ ሥርአት ዛሬ ተፈጽሟል።
የድምጻዊቷ የቀብር ሥነ ሥርዓት ቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድ እና የጥበብ አፍቃሪያን በተገኙበት ተፈፅሟል።
ድምፃዊቷ ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ በዓለማዊ ሙዚቃና በመንፈሳዊ መዝሙሮች ሀገሯንና ሕዝቧን ማገልገሏ በህይወት ታሪኳ ላይ ተገልጿል።
መስከረም 28/ 1935 ዓ.ም የተወለደችው ድምጻዊት ሂሩት ከ1950 ዎቹ መጀመሪያ እስከ 1980ዎቹ መጨረሻ ድረስ በርካታ የሙዚቃ ሥራዎችን ለአድማጭ አበርክታለች።
ከዳህላክ፣ ዳሽን እና ዋልያስ ባንድ ጋር በርካታ ሥራዎችን የሠራችው አርቲስቷ ፥ ለ35 ዓመታት ያክል በፖሊስ ሠራዊት የሙዚቃና ቴአትር ክፍል ነበር ያገለገለችው።
በእነዚህ 35 ዓመታትም ከ200 በላይ ሙዚቃዎችን አበርክታለች። ከ38 ሙዚቃዎች በላይ በሸክላ እንዲሁም ከ14 አልበሞች በላይ በካሴት መታተማቸው የታሪክ ማህደሯ ያስረዳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ከውጪም ከሀገር ውስጥም የተለያዩ ከፍተኛ ሽልማት ተበርክቶላታል።
ከ1987 ጀምሮ ለ25 ዓመታት በላይ በቤተ ክርስቲያን ስታገለግል ሦስት የመዝሙር አልበሞችን አበርክታለች።
ድምጻዊቷ የሰባት ልጆች እናት የአስር ልጆች አያትና የሰባት ልጆች ቅድመ አያት ነበረች።
ድምፃዊቷ ባደረባት ህመም ምክንያት በህክምና ስትረዳ ቆይታ ባሳለፍነው ግንቦት አራት በ 80 ዓመቷ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቷ አይዘነጋም።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!