
ባሕር ዳር: ግንቦት 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜኑ ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት በትላልቅ ድልድዮች ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል። በሰሜን ወሎ የሚገኘው የአልውኃ ድልድይ፣ እብናትና ደሃናን የሚያገናኘው የተከዜ ድልድይ፣ ሰቆጣና ኮረምን እንዲሁም ሰቆጣና ፃግብጅን የሚያገናኙት የጥራሪ ድልድዮችን ለአብነት ማንሳት ይቻላል።
ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ሰቆጣን ከፃግብጅ ጋር ከሚያገናኘው የጥራሪ ድልድይ ውጭ ያሉት ድልድዮች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ ከአማራ ክልል መንገድ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የፃግብጅ ወረዳ አስተዳዳሪ ንጉሱ ደሳለኝ እንደነገሩን የጥራሪ ድልድይ የፃግብጅ ወረዳን ከሰቆጣ ጋር የሚያገናኝ ብቸኛ ድልድይ ነው። ድልድዩ ባለመጠገኑ የበልግ ወቅትን መግባት ተከትሎ በጣለው ዝናብ ማኅበረሰቡን መልሶ ለማቋቋም፣ ድጋፎችን ለማቅረብ፣ የወደሙ የመንግሥት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት፣ የንግድ ሥራዎችን ለማከናዎንና የአካባቢውን ሰላም ለማስከበርም ፈተና ሆኗል።
ጉዳዩን ለዞን መንገድ መምሪያ እና ለአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ማቅረባቸውን አንስተዋል።
ችግሩን ፈጥኖ መፍታት ካልተቻለ ማኅበረሰቡ የከፋ ችግር ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ነው የገለጹት።
የዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር መንገድ መምሪያ ሥራ አሥኪያጅ ሰለሞን እሸቱ እንዳሉት ፃግብጅ ወረዳን ከሰቆጣ ጋር የሚያገናኘው ብቸኛው ድልድይ ባለመሠራቱ ሦሥት ተሽከርካሪዎች በጎርፍ ተወስደዋል። በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይም ተጽዕኖ አሳድሯል። ፈጥኖ እንዲገነባም ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ የኮንስትራክሽንና ኮንትራት አስተዳደር ዳይሬክተር ምህረት እውነቴ እንዳሉት ከሰቆጣ ፃግብጅ የሚወስደው ድልድይ ለመገንባት መሰሶዎችን የማስተካከል ሥራ ተሠርቷል። በቅርቡም የብረት መገጣጠሙ ሥራ ተጠናቅቆ አገልግሎት እንደሚጀምርም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!