በ2015 ዓ.ም አረንጓዴ አሻራ በምሥራቅ ጎጃም ዞን 27 ሺህ 652 ሄክታር መሬት በደን እንደሚሸፈን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ።

222

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በ2015 ዓ.ም አረንጓዴ አሻራ በምሥራቅ ጎጃም ዞን 27 ሺህ 582 ሄክታር መሬት በደን እንደሚሸፈን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገልጿል። የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ አቶ ፈንታሁን ቸኮል የበጋ አፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች በሁሉም አካባቢዎች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በበጋ የተሠሩ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራዎችን በክረምቱ የአረንጓዴ አሻራ ሥራ በመድገም በሥነ ሕይወታዊ ዘዴ የታገዘ ለማድረግ የመሬት ልየታ ዘግጅት መጠናቀቁንም ጠቁመዋል።

አቶ ፈንታሁን የተለየው መሬት በደን እና በጥምር ደን ይሸፈናል ነው ያሉት። በደን ልማት 9 ሺህ 873 ሄክታር መሬት ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ ሲኾን በጥምር ደን ደግሞ 17 ሺህ 709 ሄክታር መሬት ይሸፈናል ተብሏል።

መምሪያ ኀላፊው በደን እና በጥምር ደን የሚለማው መሬት  ከወዲሁ ተለይቶ ችግኝ በመዘጋጀት ላይ እንደኾነ ተናግረዋል። የሚዘጋጀው ችግኝ በቂ እና ጤናማ እንዲኾንም ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።

የተለየውን መሬት ለመሸፈን 252 ሚሊዮን ችግኝ እንደሚያስፈልግ ታቅዶ እየተሠራ ነው። ከዚህ ውስጥ እስከ ሚያዚያ ወር መጨረሻ ድረስ ወደ 206 ሚሊዮን በቆጠራ የተረጋገጠ ችግኝ ዝግጁ መኾኑን አቶ ፈንታሁን ተናግረዋል።

ከተዘጋጀው መሬት ውስጥ 27 ሺህ ሄክታሩ በአንድ ጀንበር በችግኝ የሚሸፈን ሲኾን ለዚህም 28 ሚሊዮን ችግኝ ተዘጋጅቷል።

በዞኑ የአረንጓዴ አሻራ ተሳትፎ በየዓመቱ እየተሻሻለ እንደመጣ የጠቀሱት መምሪያ ኀላፊው የሚተከለውን ችግኝ የመጽደቅ ምጣኔ ለመጨመር በልዩ ትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑም ተናግረዋል። የተተከሉ ችግኞች በአስተማማኝነት እንዲጸድቁ እና ጤንነታቸው የተጠበቀ እንዲኾን ፍሉ በፕላስቲክ ቱቦ ውስጥ መፈላት አለበት። በዞኑ በዚህ ዓመት ከተዘጋጀው አጠቃላይ የችግኝ ፍል ውስጥ 151 ሚሊዮን የሚኾነው በፕላስቲክ ቱቦ የተዘጋጀ ነው።

ከፍተኛ የኾነ በጀት፣ የሰው ኀይል እና ጊዜ የሚጠይቅ በመኾኑ ሁሉንም ችግኞች በፕላስቲክ ቱቦ ማፍላት አለመቻሉን አቶ ፈንታሁን ተናግረዋል። እንደ አማራጭም ደረጃውን የጠበቀ መደብ በማዘጋጀት ቀሪ ችግኞች መፈላታቸውን መምሪያ ኀላፊው ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በምሥራቅ ጎጃም የተተከለው ችግኝ የመጽደቅ ምጣኔ 80 በመቶ እንደነበር የዞኑ ግብርና መምሪያ መረጃ ያመለክታል። በዚህ ዓመትም የተሻለ የመጽደቅ ምጣኔ እንዲኖር በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑ አቶ ፈንታሁን ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article “ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከልሂቃንና ፖለቲከኞች በተጨማሪ ሕዝቦች በሀገራቸው ጉዳይ ሀሳብ እንዲሰጡ ለማስቻል እየሰራ ነው ” ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ
Next articleየቴክኖሎጅ ትውውቅ እና ሽግግር ዓውደ ጥናት የድርጊት መርኃ ግብር በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።