ባሕር ዳር፡ ሕዳር 08/2012 ዓ.ም (አብመድ) ለ60 ዓመቱ ሱዳናዊ አርሶ አደር ኦስማን ኢድሪስ የዓባይ ወንዝ አመፀኛ ነው፤ የወንዙ ውኃ መጠን ሳይታሰብ ይጨምርና የአርሶ አደሮችን ሰብልና ቤታቸውን ያጥለቀልቃል፤ ጠራርጎም ይወስዳል፡፡
“ዛሬ ምሽቱን የወንዙ የውኃ መጠን አነስተኛ ሊሆን ይችላል፤ ነገ ሳይታሰብ ሞልቶ ቤቶችን ሊያጥለቀልቅ ይችላል፤ ሞገደኛ ወንዝ ነው” ብለዋል ኢድሪስ አስተያዬት ሲሰጡ፡፡
እንዲህ ሳይታሰብ ቤት እና ንብረታቸውን እያጥለቀለቀ ላሳቀቃቸው ለእነ አርሶ አደር ኢድሪስ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለችው ግድብ ሱዳንን ከጎርፍ መጥለቅለቅ እንደሚገላግል አርሶ አደሮቹ ተስፋ አድርገዋል፡፡
በዚህ ዓመት ብቻ ዓባይ ሱዳን መሬት ላይ ባስከተለው ጎርፍ ከ60 በላይ ሰዎችን ሕይወት ነጥቋል፤ 12 ደግሞ ቆስለዋል፡፡ ወንዙ በግብፅ በኩል እስከ ሜዴትራንያን ባሕር ድረስ በሚያደርገው ጉዞ በተለይ ከካርቱም በታች የከፋ ጉዳት ያደርሳል፡፡ በካርቱም ወጣ ብላ በወንዙ ዳርቻ ጁርፌ ጋርብ በተሰኘች ትንሽ መንደር ለሚኖሩ ለእነእድሪስ ስጋቱ ትልቅ ነው፡፡
እነ አርሶ አደር እድሪስ በግድቡ እውን መሆን ተስፋ ያድርጉ እንጂ ግብጽ ግንባታው ከተጀመረ 2012 (እ.አ.አ) የውኃውን መጠን ይቀንስብኛል እያለች ስጋቷን እየገለጸች ነው፡፡ የግብጽ 90 በመቶ የንፁህ መጠጥ ውኃ እና የመስኖ እርሻ ሥራ በዓባይ ወንዝ ውኃ ጥገኛ ነው፡፡ በ1929 እና 1959 (እ.አ.አ) በወንዙ አጠቃቀም ላይ የተደረጉ ስምምነቶችን እንደ ማረጋገጫ በማንሳትም የታሪካዊ ባለመብትነት ጥያቄ ታነሳለች፤ ዳሩ ስምምነቶቹ ኢትዮጵያ ያልተሳፈችባቸውና የማትቀበለው ቢሆንም፡፡
ጉዳዩን ለመፍታት በርካታ ዙሮች ከተሄዱ በኋላ ባለፈው ወር በአሜሪካ ዋሽንግተን በግብፅ፣ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል አዲስ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ግድቡን ኢትዮጵያ አሁንም በርካታ የኤሌክትሪክ ኃይል ያላገኘ ሕዝቧን ተጠቃሚ ለማድረግና ለኢኮኖሚያዊ ዕድገቷ አስፈላጊ እንደሆነ አጥብቃ በመረዳት ከአራት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ መድባ እየገነባች ነው፡፡
የሱዳን አርሶ አደሮች ደግሞ ግድቡ ካልታሰበ ጎርፍ አደጋ እንደሚታደጋቸው ተስፋ አድርገውበታል፡፡ ባለፉት ዓመታት በዓባይ ወንዝ ዳርቻ እርሻዎች ባለቤት የሆኑት እንደ ኢድሪስ ያሉ አርሶ አደሮች የጎርፍ መጥለቅለቅ የሚፈጥረው ደለል የሰብል እርሻቸውን ወደ እንስሳት መኖ እንዲቀይሩ አስገድዷቸዋል፡፡
ሌላው ችግር ደግሞ ጡብ ሠሪዎች በወንዙ ዳርቻ ጡቡን ለመጥበስ በሚያደርጉት ሂደት ሰብሎች ላይ ጉዳት የሚያደርስ ጭስ ይፈጥራሉ፡፡ እናም “ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን ከማልማት ወደ የእንስሳት መኖነት ለመለወጥ ተገድደናል” ይላሉ አርሶ አደሩ እንድሪስ፡፡
እናም በጎርፉ ምክንያት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ እና የተወሰኑ ሰብል ዓይቶችን ብቻ ለማምረት ተገድደዋል፡፡ የወንዙ ፍሰት የተስተካከለ ቢሆን ግን የተሻለ የእርሻ ሥራ ይሠራ ነበር ባይ ናቸው፡፡ “ለሰብል እርሻችን እናቅዳለን፣ ለአካባቢዉም ለገበያውም የተሻለ ይሆን ነበር፤ ትርፋማ እንሆን ነበርም” ብለዋል፡፡
በካርቱም አል-ዛኢም አልዛሃሪ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ኤክራም ዳጋሽ ሱዳን ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠቃሚ እንደምትሆን ይስማማሉ፡፡ የውኃውን መጠን በመቆጣጠር የጎርፍ መጥለቅለቁን ያስቀራል ባይም ናቸው፡፡
እንደ ፕሮፌሰሯ አስተያዬት ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባበት ብቸኛው ምክንያት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ለአጎራባች አገራት ብሎም ለመላው አፍሪካ አህጉር ለመላክ ነው፡፡
በሱዳን በግድቡ ስጋት ሚያድርባቸው ጡብ ሰሪዎች ብቻ ናቸው፡፡ እንደ ያዕቆብ ኖሪን በመቶዎች የሚቆጠሩ በወንዙ ዳርቻ ከሚፈጠረው ደለል ጡብ በመሥራት የሚተዳደሩ ሰዎች ገቢያቸው ሊቀንስ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው፡፡ ፕሮፌሰር ኤክራም ዳጋሽ ግን የግድቡ ጠቀሜታ ከዚያም በላይ ነው ባይ ናቸው፡፡ እነ ያዕቆብ ሌላ የሥራ አማራጭ ሊፈልጉ እንደሚችሉ በማመላከት፡፡
ግድቡ የዉኃውን ፍሰት ሲቆጣጠር በደለል የሚሸፈኑ መሬቶች ለእርሻ እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ፕሮጄክቶች ክፍት ይሆናሉ ብለዋል ፕሮፌሰሯ፡፡ በተጨማሪም ግድቡ ሱዳን በተመጣኝ ዋጋ “የኤሌክትሪክ ኃይል እንድታገኝ ያደርጋታል፤ ይህ ደግሞ የሀገሪቱን እድገት ይጨምራል” ብለዋል ፕሮፌሰሯ፡፡
ምንጭ፡- ፍራንስ 24
በየማነብርሃን ጌታቸው