“ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከልሂቃንና ፖለቲከኞች በተጨማሪ ሕዝቦች በሀገራቸው ጉዳይ ሀሳብ እንዲሰጡ ለማስቻል እየሰራ ነው ” ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

93

ባሕር ዳር ፡ ግንቦት 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሕዝቦች ከልሂቃንና ፖለቲከኞች በተጨማሪ በሀገራቸው ጉዳይ ሀሳብ እንዲሰጡ ለማስቻል እየሰራ መሆኑን የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።

የምክክር ኮሚሽኑ ከኦሮሚያ ክልል ምሥራቅና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋና ምሥራቅ ቦረና ዞኖች ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ እየመከረ ይገኛል።

በመድረኩ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንደገለጹት ኮሚሽኑ ከልሂቃንና ፖለቲከኞች በተጨማሪ ሕዝቦች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ሀሳብ እንዲሰጡ ለማስቻል እየሰራ ነው።

የዛሬው መድረክም ባለድርሻ አካላት በተሳታፊዎች ልየታና በአጀንዳ ማሰባሰብ ዙሪያ ግልጽ ግንዛቤ እንዲይዙና በምክክሩ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማስቻል ነው ብለዋል።

በመድረኩ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አረጋውያን፣ የሲቪክና ሕዝባዊ ተቋማት፣ የፖለቲካ አካላት የሚሳተፉበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ሁሉም ተሳታፊዎች በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳዎች ላይ ግብዓት እንዲሰጡ የተዘጋጀ እንደሆነም ገልጸዋል።

”ሁሉም ስለ ሀገሩ ሀሳብ መስጠት አለበት” ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ሀሳብ በማውጣት በምክክር ወደ አንድ ለማምጣት መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም የምክክር ሂደቱ ከአጀንዳ አሰባሰብ ሂደቱ ጀምሮ አካታችና አሳታፊ እንዲሆን ኮሚሽኑ በሙሉ አቅሙ እየሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ፈተናን ወደ ዕድል የሚቀይሩ ነገን የተሻለ ለማድረግ የሚሠሩ ሴት መሪዎችን ማፍራት  ያስፈልጋል” አቶ መለሰ ዓለሙ
Next articleበ2015 ዓ.ም አረንጓዴ አሻራ በምሥራቅ ጎጃም ዞን 27 ሺህ 652 ሄክታር መሬት በደን እንደሚሸፈን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ።