
👉የብልፅግና ሴቶች ሊግ የአሰልጣኞች ስልጠና በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሔደ ነው።
አዲስ አበባ ፡ ግንቦት 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በስልጠና መግቢያ ላይ ሃሳብ የሠጡት የብልፅግና የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪክ ባሕል ግንባታ ኃላፊ አቶ መለሰ አለሙ ወደ አሰብነው ብልፅግና ለመጓዝ በትጋት እየሠራን መጓዝ ይጠበቅብናል ብለዋል። በዚህ ትጋት ውስጥ ደግሞ መሪ መቅረፅ ፣ ማሳደግ እና ዕድል መሥጠት ተገቢ ነው ብለዋል።
ብልፅግና የአንድ ጊዜ ሳይኾን የትውልድ ፓርቲ በመኾኑ በዚህ የትውልድ ግንባታ ደግሞ የሴቶቸ ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ መለሰ የብልፅግና የሴቶች ሊግ ሚና በፓርቲው ፕሮግራም በግልጽ ተቀምጧል።
ፈተናን ወደ ዕድል የሚቀይሩ ነገን የተሻለ ለማድረግ የሚጥሩ ሴት መሪዎችን ማፍራት ያስፈልጋል ብለዋል አቶ መለስ። ይህንን ማድረግ የሚችሉ 2000 ሴት መሪዎችን ለማፍራት ፓርቲው ፕሮግራም ይዞ እየሰራ ነው። የሴቶች ሊግ ደግሞ የአመራር ቋት ነው ብለዋል።
እንደ አቶ መለሰ ገለጻ ይህ የሊግ ስብሰባ የአሰልጣኞች ስልጠና ሲኾን በቀጣይ በየደረጃው 2000 የብልፅግና ሊግ አባላት ስልጠና ይወስዳሉ።
በፖለቲካው ዘርፍ መሪ የማብቃት ዕቅድ ያለው ስልጠና ቢኾንም በቀጣይ በፖለቲካ ብቻ ሳይኾን በኢኮኖሚ፣ በማኀበራዊ እና በሌሎች ዘርፎች መሪዎችን የማብቃት ዕቅድ መኖሩን አመላክተዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ኃላፊ ወይዘሮ ዘሀራ ሁመድ በበኩላቸው በዚህ የአስጣኞች ስልጠና ከአሰልጣኞች ትምህርት እና የህይወት ተሞክሮ የሚወሰድበት መኾኑን አንስተው የአመራር ክህሎትን የምናዳብርበት ትልቁ ዓላማ ያለው ነው ብለዋል።
በስልጠናው ከሁሉም ክልል እና ከተማ አሥተዳደሮች የተውጣጡ 130 አሰልጣኞች ስልጠና ይወስዳሉ ተብሏል።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
