“በአንድ እጃችን እያለማን በሌላኛው ክንዳችን የአካባቢያችንን ሰላም እያስጠበቅን ምርታማነታችንን አሳድገናል” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ

368

ሁመራ: ግንቦት 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳደር በዞኑ ከሚገኙ አልሚ ባለሃብቶች ጋር የአካባቢ ሰላም ማስጠበቅና በ2015/16 የምርት ዘመን የእርሻ ዝግጅት ላይ በሁመራ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱም በርካታ አልሚ ባለሃብቶች ተገኝተዋል። በምርት ዘመኑ ከግብዓት አቅርቦት ጀምሮ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ባለሀብቱ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ምርታማ መኾኑ ተገልጿል።

በዞኑ ከ427 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በተለያዩ ሰብሎች የለማ ሲኾን ከዚህም ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱ ተመላክቷል።

በውይይቱም በባለፈው የምርት ዘመን የነዳጅ ፣ የኬሚካል አቅርቦትና ሌሎች ለሰብል ልማት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በወቅቱ አለመቅረብ ችግር ፈጥሮባቸው እንደነበር አልሚ ባለሃብቶች አንስተዋል።

ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ያመረቱት ምርት የገበያ ችግር እያጋጠማቸው መኾኑን የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል። በ2015/16 የምርት ዘመን የገበያ ችግር እንዳያጋጥመን ከወዲሁ ሊሠራበት ይገባል ብለዋል።

ከነጻነት ማግስት ተጠቃሚ ነን ያሉት አልሚ ባለሃብቶቹ በመጭው የምርት ዘመን ይበልጥ ውጤታማ ለመኾን ዝግጅት እያደረጉ መኾኑን ተናግረዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና ልማት መምሪያ ኀላፊ አወቀ መብራቱ በመጭው የምርት ዘመን ከ500 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በዘር ለመሸፈን መታቀዱን ገልጸዋል።

የግብዓት አቅርቦቶችን በወቅቱ ተደራሽ ለማድረግ ከክልል ግብርና ቢሮ ጋር በቅርበት እየተሠራ ነው ብለዋል። ባለ ሃብቶች በመሬታቸው ላይ የተለያየ ሰብልን በመዝራት የገቢያ ችግር እንዳያጋጥማቸው እንደ አማራጭ ሊጠቀሙ ይገባል ብለዋል።

እያጋጠሙ ያሉ የገቢያ ችግሮችን ለመቅረፍ ከክልል መንግሥት ጋር በቅርበት መሠራቱን አንስተዋል። በቀጣይም የገበያ ችግር እንዳይፈጠር በትኩረት እንሠራለን ነው ያሉት።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የዞኑ አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ባለሃብቶቹ የአካባቢው ሰላም ለማስጠበቅ እያደረጉት ያለው ድጋፍና ክትትል የሚደነቅ በመኾኑ አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።

በዞኑ በሕዝብ ተሳትፎ የተጀመሩ መሠረተ ልማቶችን ለማስቀጠል አልሚ ባለሃብቶች በርካታ ድጋፎችን እያደረጉ መኾኑን ገልጸዋል።

በዞኑ በአንድ እጅ እያለማን በሌላኛው ሰላማችንን እያስጠበቅን ምርታማነታችንን አሳድገናል ያሉት አቶ አሸተ በቀጣይም የአካባቢያችንን ሰላም በማስጠበቅና እርስ በእርስ በመደጋገፍ ልማታችንን ልናስቀጥል ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ – ያየህ ፈንቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በሁከትና ትርምስ ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለማሳካት የሚደረግ ሙከራ ጉም እንደመጨበጥ ነዉ” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
Next articleበኩር ጋዜጣ ግንቦት 07/2015 ዓ.ም