
ባሕር ዳር: ግንቦት 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የሰጠውን ሳምንታዊ መግለጫ ሙሉ መልእክት ቀጥሎ ቀርቧል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ዉስጥ ከገባች አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህ የለዉጥ
ዓመታት ይኾናል ተብሎ ያልታሰቡ በርካታ ድሎች ተመዝግበዋል፡፡ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ
ዘርፎች ሀገራችንን ወደፊት ሊያስፈነጥሩ የሚችሉ በአለት ላይ የተገነቡ መሰረቶች ተጥሏል፡፡ ኾኖም ግን
የተገኙ ስኬቶች አልጋ በአልጋ በኾነ ኹኔታ ውስጥ አልተመዘገቡም፡፡ ይልቁንም በርካታ ፈተናዎችን
በመሻገር የተገኙ ውጤቶች ናቸው፡፡
ለውጡ ገና ከመነሻዉ እንዲጨናገፍ መጠነ ሰፊ ሴራዎች ተሸርበዉ ለውጡን ለማጠልሸትና የለውጥ
አመራሩን ተስፋ ለማስቆረጥ ጥቃቶች ተሰንዝሯል፤ የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ተከፍቷል፡፡ የብርቅዬ
አመራሮችና ዜጎች ሕይወት ተቀጥፈዋል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች ከቤት ንብረታቸዉ
ተፈናቅለዋል፡፡ ጦርነት ተከፍቶ የበርካቶችን ሕይወት በልቷል፡፡ በአጠቃላይ ሀገርና ሕዝብን ከፍተኛ ዋጋ
አስከፍሏል፡፡ የእነዚህ ጥፋቶች መነሻቸው በአንድም በሌላም ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድና በንግግር
ከመፍታት ይልቅ የአንድን ቡድን ጠባብ ፍላጎት በሌላዉ ላይ በኀይል ለመጫን ከመፈለግ የሚመነጭ
ነዉ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገራችን በዓይነቱና በዲሞክራሲያዊነቱ ልዩ በኾነዉ ምርጫ ይኾነኛል ያለውን
ፓርቲ በመምረጥ ሕገ-መንግሥታዊና ዲሞክራሲያዊ መንግሥት እንዲመሰረት አድርጓል፡፡ በመኾኑም
ጉልበትና ትርምስ ከእንግዲህ ወዲህ ለሥልጣን እንደማያበቁና ጠብመንጃ የመንግሥት ሥልጣን ምንጭ
የሚኾንበት ምዕራፍ እንዲዘጋ ኾኗል፡፡
ኾኖም ግን ኢትዮጵያ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ልምምድ ሂደት ዉስጥ በመግባቷ በሐሳብ ብልጫና
በምርጫ ለማሸነፍ ያልቻሉና ተስፋ የቆረጡ ቡድኖች በብሔርና በሰፈር ማንነት እየማለ ጽንፈኛ
አስተሳሰብን በማቀንቀን መንግሥትን በኀይል ለማንበርከክ ያልቆፈሩት ጉድጓድና ያልተጓደኙት ኀይል
የለም፡፡ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በጽንፈኝነት አስተሳሰብ የተደራጁ ቡድኖች የሕዝብን ሰላም እና
ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል ተንቀሳቅሰዋል፡፡ እነዚህ እኩይ ኀይሎች በኾነ ጊዜ በብሔር መብት
አስጠባቂነት፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ በሃይማኖት መብት አስካባሪነት ስም ቢንቀሳቀሱም፤ ዓላማቸዉ በሐሳብ
ተወዳድሮ ሊጨብጡ ያልቻሉትን የመንግሥት ሥልጣን በኀይል መቆጣጠር ነዉ፡፡
የእኩይ ዓላማቸዉ ማስፈጸሚያ ስልት አድርጎ የቀየሱት መንገድ ደግሞ አንድን ብሔር ተበዳይ፣ ሌላውን
በዳይ አድርጎ በመሳልና በሕዝቦች መካከል መጠራጠርን፣ ግጭትና ያለመተማመንን ስሜትን በመፍጠር የጋራ እሴቶቻችንን በመሸርሸር ነዉ፡፡ አካሄዳቸዉም በተግባር ከሚፈጽሙት አስነዋሪ ድርጊት ባሻገር እጅግ አሳፋሪና ለኢትዮጵያዊያን ባህል፣ እሴትና ሥነ-ምግባር የማይመጥን የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ሲነዙ
ተስተውሏል፡፡
እነዚህ ጽንፈኛ ኀይሎች ከራሳቸዉ ጥቅምና የሥልጣን ጥማት ውጪ የማንም ብሔር ኾነ ሃይማኖት
ወኪል አይደሉም፡፡ አንዱን ቅዱስ ሌላውን አርዮስ በማድረግ፤ ንፁሀንን እየጨፈጨፉ፤ የመንግሥት
ኀላፊዎችን እየገደሉ፤ የቁርጥ ቀን ዋስትናችን፣ የሕዝብ መከታ በኾነዉ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ
ጥቃት እየፈጸሙ እና የተረጋጋ ሀገረ መንግሥት እንዳይኖር እየሠሩ ያሉት እነዚህ አካላት የየትኛዉም
ብሔር ወኪል ሊኮኑ አይችሉም፡፡ በመኾኑም ሕገወጥ ድርጊት እየፈጸሙ በብሔሮች ጉያ ውስጥ
ለመደበቅ የሚሞክሩትን ጽንፈኞች ሕዝባችን ሊታገላቸው ይገባል፡፡ የትኛውም አይነት ጥያቄና ፍላጎት
ከወንድማማችነት፣ አብሮነትና እኩልነት ውጪ ሊሳካ እንደማይችል ሁሉም መገንዘብ ይኖርበታል፡፡
መንግሥት ከየትኛውም ጊዜ በላቀ ኹኔታ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊና ሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝምን
ተግባራዊ በማድረግ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት፣ ፍትሓዊነትና እኩልነት እንዲረጋገጥ በተግባር እያረጋገጠ ባለበት ኹኔታ በኀይልና በጉልበት የራስን እኩይ ፍላጎት በሌሎች ላይ በመጫን የትኛዉንም አይነት
ፍላጎትም ኾነ ጥቅም ማረጋገጥ እንደማይቻል ሊገነዘበው ይገባል።
መንግሥትም የጸጥታ መዋቅሮችን በማጠናከር፣ አንድ ጠንካራ መከላከያ ሠራዊትን በመገንባት በሀገሪቱ
ያሉ የጸጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ይገኛል፡፡ የክልሎችን የጸጥታ
አካላት መልሶ በማደራጀት አንድ ጠንካራ ሀገራዊ ሠራዊት በመገንባት የመላ ሕዝባችንን ደህንነትና ሰላም
ለማረጋገጥ የጀመረውን ሥራም አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
የትኛዉንም አይነት ጥያቄ በዉይይትና በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንዲቻል በተለያየ ምክንያት
ጠብመንጃ አንግቦ ለሚንቀሳቀሱ አካላት መንግሥት ያቀረበዉ ሰላማዊ አማራጭ አወንታዊና የተሳኩ
ውጤቶች እየተገኙበት ነዉ፡፡ ከዚህ አንፃር በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት በሰላም ስምምነት
ከመቋጨትም ባለፈ በጋምቤላ፤ በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በሌሎችም ክልሎች ከመንግሥት የጸጥታ
ኀይሎች ጋር የሽምቅ ውጊያ ሲያደርጉ የነበሩ በርካታ ታጣቂዎችንም ወደ ሰላማዊ ጎዳና በመመለስ
የተሀድሶ ፕሮግራም እያከናወነ ይገኛል፡፡
አሁን ባለው የሀገራችን ተጨባጭ ኹኔታ በሀሳብ ልእልና ተወዳድሮ እና ሀሳብን ለመራጩ ሕዝብ አቅርቦ ማሸነፍ እየተቻለ በአፈሙዝ ሥልጣንን ለማግኘት የሚደረግ ሩጫ ለክፍለዘመኑ የማይመጥን እንዲሁም ተሞክሮ የከሸፈ በመኾኑ፣ ከሀሳብ ልእልና ውጪ ወደ ሥልጣን መምጣት እንደማይቻል መገንዘብ ይገባል፡፡
የሀገራችንን ሰላም እና ጸጥታ በማናጋት የሚሳካ የፖለቲካ ግብ ከእንግዲህ እንደማይኖር መታወቅ ይኖርበታል፡፡ አካሄዱም መጨረሻውም ኪሳራ ብቻ መኾኑን ከራሳችን ያለፉ ተሞክሮዎች መማርና መገንዘብ ያስፈልጋል።
መንግሥት በሀገራችን መንፈስ የጀመረው የሰላም አየር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ካለው ፅኑ አቋም አንፃር
ጽንፈኛ ኃይሎች የሚወስዷዋቸውን እርምጃዎች በትዕግስት ሲያልፍ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ጽንፈኛ
ኀይሎች መንግሥት የሚያሳየውን ትዕግስት እንደፍርሀት በመቁጠር ዛሬም በጥፋታቸው ቀጥለውበታል፡፡ መንግሥት በተደጋጋሚ እንደገለጸው ለየትኛዉም የሐሳብ ልዩነት ጠብመንጃ ማንሳት ሳይኾን ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ቅድሚያ የሚሰጥ ቢኾንም የሕዝብን ሰላም እና ደህንነት ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ኀይሎች ላይ ግን ሕግ የማስከበር እርምጃውን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ሕዝባችንም የጽንፈኞችን ሀገር አፍራሽ ተግባር በመገንዘብ እንደተለመደው ከመንግሥት ጎን በመቆም ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የሚጠበቅበትን ሁላ እንዲወጣ መንግሥት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
ሚያዝያ 6/2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
