በአማራ ክልል በግንባታ ላይ የሚገኙ ዘጠኝ ድልድዮችን በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የክልሉ መንገድ ቢሮ ገለጸ።

98

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች ላይ በሚገኙ ወንዞች የመሻገሪያ ድልድይ ሳይገነባ በመቆየቱ የማኅበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ግንኙነት እንዲቋረጥ ማድረጉን መነሻ በማድረግ በበጀት ዓመቱ 23 ነባርና አዲስ የኮንክሪት ድልድዮች ለማስገንባት ታቅዶ የሥራ ስምሪት መሰጠቱን የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ለአሚኮ በላከው መረጃ ገልጿል።

በተደጋጋሚ በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ጥያቄ ሲነሳባቸው የነበሩ ድልድዮችን ለይቶ ምላሽ ለመስጠት የክልሉ መንግሥት በልዩ ትኩረት አስፈላጊውን የካፒታል በጀት የመደበ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ሰባቱ በነባር የዩራፕ መንገድ ላይ የሚገነቡ አዲስ የኮንክሪት ድልድይ ፕሮጀክቶች ናቸው።

እነዚህን ፕሮጀክቶች ባለፉት 90 ቀናት ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ አፈፃፀማቸውን በተገባው ቃል መሰረት ለማጠናቀቅና ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ እየተከናወኑ ይገኛሉ። በዚህም መሰረት ግንባታዎቹ በአማካኝ 70 በመቶ የአፈፃፀም ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ቢሮው ገልጿል።

አነዚህ ፕሮጀክቶችም፦
👉 በምዕራብ ጎጃም ዞን ደቡብ አቸፈር ወረዳ የአሻር ወንዝ ድልድይ
👉 በምዕራብ ጎጃምና አዊ ዞን ዓባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው የዓባይ ድልድይ
👉 በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞን ጓንጓ ወረዳ የችክሲ ወንዝ ድልድይ
👉 በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሰዴ ወረዳ የተፌ ወንዝ ድልድይ
👉 በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ የለምለም ተራራ ወንዝ
👉 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምዕራብ በለሳ ወረዳ የደባሪ ወንዝ ድልድይ
👉 በደቡብ ጎንደር ዞን መቀጥዋ ወረዳ ማላ ወንዝ ላይ የሚገነባው የኮንክሪት ድልድይ
👉 በደቡብ ወሎ ዞን አርጎባ ወረዳ የሰውሰዋ ወንዝ ድልድይ እንዲሁም
👉 በሰሜን ሸዋ ዞን አንኮበር ወረዳ የአይራራ ወንዝ ድልድይ ናቸው።

እነዚህን ለአብነት ያህል ተጠቀሱ እንጂ በቀሪዎቹ ዞኖችም ነባርና አዲስ ድልድዮችን ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል።

የድልድይ ፕሮጀክቶቹን በምህንድስና ዘርፍ ተመርቀው ከተደራጁ ኢንተርፕራይዞችና አማካሪዎች ጋር ውል በመውሰድ በመልካም አፈፃፀም ላይ የሚገኙ ናቸው።

የአካባቢው አመራርና ማኅበረሰብም ለፕሮጀክቶቹ እያደረገ ያለው ክትትል፣ ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቢሮው አሳስቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአንድ ነጥብ አምስት ቢልዮን ብር ያስመዘገቡ 126 ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ባለሐብትነት ተሸጋገሩ።
Next article“በሁከትና ትርምስ ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለማሳካት የሚደረግ ሙከራ ጉም እንደመጨበጥ ነዉ” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት