“የውበት ሠገነት፣ ተወዳጅ እመቤት”

85
Made with LogoLicious Add Your Logo App

ባሕር ዳር: ግንቦት 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የቆላው አቀበቱን ወጥቶ የሚያርፍባት፣ የደጋው ቁልቁለቱን ወርዶ የሚገናኝባት፣ የደከመው ብርታት የሚያገኝባት፣ የራበው የሚጎርስባት፣ የጠማው የሚጠጣባት፣ የቀደመ ታሪክ የሚነገርባት፣ ነገሥታቱ የተመላለሱባት፣ አያሌ ታሪኮችን የሠሩባት፣ ለስማቸው ማስታወሻ አሸራቸውን ያስቀመጡባት፣ የውበት ሠነገነት፣ ተወዳጅ እመቤት የሆነች ውብ ሥፍራ፡፡

በዙሪያዋ ማርና ወተት መልቶባታል፣ አብያተክርስቲያናት እና ገዳማት ይከቧታል፣ ምስጢራዊ ሐይቅ ጣና ያጅባታል፣ ውበትና ግርማን ሰጥቷታል፣ ታሪክና ሃይማኖት ይነገርባታል፣ ኩሩና ጀግና ይወለድባታል፣ በኩራትና በክብር ይኖርባታል፡፡ ፍቅርን እንደ ጣና ያሰፋች፣ ውበት እንደካባ የደረበች፣ መወደድን እንደ በትረ መንግሥት የጨበጠች፣ እንደ ኩሩ ንጉሥ በሚያምር የውበት ዙፋን ላይ የተቀመጠች፣ እንደ አማረ ቤተ መንግሥት በዙሪያ ገባዋ ግርማን እና መወደድን የተቸረች ድንቅ ምድር፡፡

ተውባ ተፈጥራለች፣ አምራ ተሠርታለች፣ ቀልብን በሚስብ ጸጋ ተከባለች፣ እንደ ልዕልት አምራ ትታያለች፣ እንደ ንግሥት በግርማ ትኖራለች፣ እንደ ንጉሥ የውበት ዘውድ ደፍታ ያያትን ሁሉ ታስቀናለች፣ በአሻገር ያለውን ሁሉ በውበቷ ትጠራለች፡፡ በሚያምር ውበቷ ታፈዝዛለች፡፡

ዘውድ እንደጫነ ንጉሥ በተፈጥሮ ተውባለች፣ ዘውድ እንደጫነች ንግሥት በአምላክ እጆች አምራለች፣ በቤተ መንግሥት አገልጋዮች እንደተከበበች ልዕልት ታማልላለች፣ የክብር ልብሳቸውን እንደለበሱ መኳንንትና መሳፍንት ታሳሳለች፡፡ በእንቁ እንደተንቆጠቆጠ ሠረገላ፣ በወርቅ እንዳጌጠ ዙፋን በውበቷ ታፈዝዛለች፡፡ ውበቷ በተፈጥሮ የተሰጣት፣ አምላክ በመልካም እጆቹ ያደላትና ያጎናጸፋት እንጂ ማንም የጨመራት አይደለም፡፡ በአምላክ እጆች ተዋበች፣ በአምላክ እጆች ጸጋን ተሰጠች፣ በውበቷም ተወደደች፡፡

ንጉሥ እስከ ሠራዊቱ ከትሞባታል፣ መኳንንትና መሳፍንት ከነገሥታቱ ጋር ታይተውባታል፣ በሐይቅ ውስጥ ባሉ ገዳማት የሚኖሩ አበው ታሪክና ሃይማኖትን አጽንተውባታል፡፡ የኢትዮጵያን ምስጢራዊነት፣ የኢትዮጵያን ታላቅነት፣ የኢትዮጵያን ኃያልነት፣ የኢትዮጵያን ቀደምትነት፣ የኢትዮጵያን ክብርና ፍቅር አስተምረውባታል፡፡

በቀደመው ዘመን ከአለፋ ጣቁሳ የሚገኘው ጤፍና ዳጉሳው፣ ወተትና ማሩ በታንኳ ይጫንባታል፣ በጣና እያለፈም ይጓዝባታል፣ ከበረሃው ከቋራና ከመተማ የሚመጣው ምርት ይራገፍባታል፣ ታንኳ ቀዛፊዎች ይሰለፉበታል፡፡ ዛሬም ዓመታት አልፈው፣ ዘመናትን ተሻግረው ታንኳ ቀዛፊዎች፣ የጀልባ ካፒቴኖች በሥሯ አይጠፉባትም ተወዳጇ ደልጊ፡፡

የደልጊ ነዋሪዎች ከጣና ጋር አይለያዩም፡፡ ጣናን አሳ ያሰግሩበታል፣ በፍቅር ይዋኙበታል፣ በውስጡ ባቀፋቸው ገዳማትና አድባራት ሃይማኖት ይማሩበታል፣ ለነብሳቸው መዳኛ ይማጸኑበታል፤ አምላክ ለምድር ፍቅርና ረድዔትን ይሰጥ ዘንድ ይለምኑበታል፡፡ ጀንበር በማለዳ ስትዘልቅ የደልጊ ነዋሪዎች በምስጢራዊ ጣና ላይ ዳር ላይ ይታያሉ፡፡ ብዙዎቹ በዚያው በጣና ዙሪያ የዕለት ተግባራቸውን ሲፈጽሙ ይውላሉ፤ ገሚሶቹ ሲዋኙ፣ ገሚሶቹ ዓሳ ሲያሰግሩ፣ ገሚሶቹ ውኃ ሲቀዱ፣ ከየብስ ወደ ሐይቅ፣ ከሐይቅ ወደ የብስ ሲመላለሱ ይታያሉ፡፡

አመሻሽ ላይ ጀንበር ስትጠልቅ ደግሞ የደልጊ ነዋሪዎች የሚወዱት ጣናን ተሰናብተውት ወደየ ማደሪያቸው ይመለሳሉ፡፡ ጨለማው ተገፍፎ፣ ብርሃን ዳግም መጥቶ፣ ሌሊቱ ነግቶ ጀንበር በምሥራቅ ታይታ ዳግም እስኪገናኙ ድረስ ጣናን ይናፍቁታል፤ እርሱም አንደበት ባይኖረው፣ ፍቅሩን እንደ እነርሱ ባይገልጸው የሚናፍቃቸው ይመስላል፡፡ ለምን ውበት እየሰጣቸው፣ ከእርሱ ጋር የሚዉሉት እንዲለዩት አይወድምና፡፡

ጀንበር ባትጠልቅና ባይለያዩ ምንኛ ደስ ባላቸው ነበር፡፡ ዳሩ ጀንበር አመሻሽ ላይ ታዘቀዝቃለች፣ ያን የመሠለ ደም ግባቷን ከልላ ምድርን ለጨለማ አስረክባ ትኮበልላች፡፡ ጨለማው ካባውን ሲጥል ጣና እና የደልጊ ነዋሪዎች እየተዋደዱ ይለያያሉ፡፡ በማግሥቱ ለመገናኘትም ቀጠሮ ይይዛሉ፡፡ እንዲህ እንደተነፋፈቁ ዘመናት አልፈዋል፡፡ ቀናት ሄደው ቀናት ተተካክተዋል፡፡ ያ ፍቅራቸው እና ትስስራቸው ዛሬም ቀጥሏል፣ ነገም እንደዚያው፡፡

ደልጊ ምንምእንኳ አምላክ እንደቸራት ውበት ሁሉ ሰዎች ባያስውቧትም፣ በመወደዷ ልክ ባያሳምሯትም፣ እንደ ታሪኳ እርዝመት ቅንጡ ከተማ ባትሆንም የበዛ ታሪክ ያለባት ውብ ሥፍራ ናት፡፡ እድሜዋ ዘለግ ብሎ የሚቆጠር፣ ታሪኳ ሰፋ ብሎ የሚነገር ናት፡፡

ታሪክ አዋቂው ገበያው በሬ ደልጊ ተስፋና ፀሐይ በሚወጣበት በምሥራቅ ጣና ግርማን የሰጣት ውብ ሥፍራ ናት ይሏታል፡፡ ወለል ያለው ሜዳ ደምቢያ በአጠገቧ ያለባት ውብ ምድር፡፡ ይህች ውብ ሥፍራ በዘመነ አምደጽዮን እንደተመሠረተች ይነገርላታል ብለውኛል፡፡ የመሠረቷትም የሀገሬው ባላባቶች ነበሩ፡፡ በዚያ በቀደመ ዘመን ጀምሮ ከዘጌ ቡና፣ ከአለፋ ጣቁሳ፣ ከደንቢያ ማርና ቅቤ በታንኳ የሚጫንባት ጥንታዊት ከተማ እንደሆነችም ነግረውኛል፡፡ ከዘጌ የሚጫነው ቡና ደልጊ ወደብ ላይ እየተራገፈ እስከ ከቋራና መተማ ይጓዝባት፣ ከደንቢያ፣ ከአለፏ ጣቁሳ፣ ከመተማና ቋራ የሚጫነው ማርና ወተት ሌላውም ወደ ዘጌ ይጓዝባት፣ ከዘጌም አልፎ ይሄድባት ነበር፡፡

በዚች ጥንታዊት ሥፍራ ደልጊ ደብረ ገነት ማርያም ትገኛለች፡፡ ይህች ቤተክርስቲያን ረጅም ታሪክ ያላት፣ ግርማና ውበት የበዛላት ናት፡፡ ደልጊ ደብረ ገነት ማርያምን ለማዬት፣ ታሪኳን ለማወቅ የሚሹ ሁሉ ይጓዙባታል፣ ከታሪኳ እየተማሩ፣ ስሟን እየዘከሩ ይመለሳሉ፡፡ በተለይም ወርኃ ጥር ደርሶ አስተርዮ በሚከበርበት ጊዜ ወደ ደልጊ ደብረ ገነት ማርያም የሚያቀናው ብዙ ነው፡፡ አስተርዮ ማርያም በጣና ዳሯ ውብ ሠፍራ፣ በደብረ ገነት ማርያም እጅግ አምሮ ይከበራልና ያን በዓል ለማዬት የሚሹ ሁሉ አስቀድመው ይጓዛሉ፡፡ ታቦቱ ከመንበሩ ሲወጣ፣ ወደ ጣናም ሲሄድ የከበረ ግርማና መወደድ አለው፡፡ በዚያ ጊዜ በደልጊ መገኘት አጀብ ያሰኛል፡፡ ያን ጊዜ በዚያ ሥፍራ መገኘት መታደል ነው፡፡

በዘመነ አምደጽዮን እና በሌሎች ነገሥታት የተሠሩ ገዳማትና አድባራት በዚያች ሥፍራ ዙሪያ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ገዳማትና አድባራትም ታሪክን እየመሰከሩ፣ ሃይማኖትን እያስተማሩ ይኖራሉ፡፡ ጥንታዊ ጎኸል ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የሚገኘውም በዚህችው ውብ ሥፍራ አቅራቢያ ነው፡፡ ይህ ጥንታዊ ቤተክርስቲያን አያሌ ታሪኮች ያሉበት ውብ ሥፍራ ነው፡፡

በዚህች ከተማ አቅራቢያ አያሌ ጦርነቶች መካሄዳቸውንም ታሪክ አዋቂው ነግረውኛል፡፡ በተለይ ደግሞ በዘመነ አጼ ዮሐንስ አራተኛ ለወረራ ከመጣው የድርቡሽ ጦር ጋር በዚሁ ሥፍራ ጀግኖች መዋደቃቸውን ነው የነገሩኝ፡፡ ለሀገራቸው፣ ለክብራቸው፣ ለሠንደቃቸው እና ለማንነታቸው መስዋእት የሆኑባት ሥፍራ እንደሆነችም ነግረውኛል፡፡

በዚያች ሥፍራ የተወለዱ ጀግኖች በየዘመናቱ የመጡ ጠላቶችን እየቀጡ መልሰዋል፣ ክብራቸውን በክንዳቸው አስከብረዋል፣ ሀገራቸውን አኩርተዋል እንጂ ማንም አላንበረከካቸውም፡፡

በዚያች ሥፍራ አቅራቢያ ስመ ገናናዋ ንግሥት እቴጌ ምንትዋብ አሻራ ይገኛል፡፡ እሳቸው እንዳሰሩት የሚነገረው የቸመራ ቁስቋም ቤተ ክርስቲያን ትገኛለች፡፡ አጼ ተዎድሮስ ሀገር ለማጽናት፣ የደከመውን ዙፋን ወደ ክብሩ ለመመለስ ባደረጉት ጦርነት ምሽግ የሠሩበት፣ ጦራቸውን ያሠፈሩበት የአጼ ቴዎድሮስ ምሽግ እየተባለ የሚጠራ ሥፍራም ይገኛል፡፡ የድርቡሽ ጦር ተነስቶ አፄ ዮሐንስ ወደ መተማ ለመዝመት በመጡ ጊዜ ከእነ ሠራዊታቸው ያረፉበት አፄ ዮሐንስ ዋርካ የሚባል ሥፍራም አለ፡፡ በውስጡ ብዙ ያልተመረመሩና ያልተደረሰባቸው ቅርሶች፣ የታሪክ አሻራዎች፣ እንደሚገኙበት የሚነገረው የእሙሃይ ዋሻ በዚህች ውብ ሥፍራ አቅራቢያ ይገኛል፡፡ ደልጊ ዙሪያዋን በታሪክ፣ በጥበብ፣ በሃይማኖት እና በውበት የተከበበች ውብ ሥፍራ ናት፡፡

ደልጊ የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም የራዕይ ከተማ ይሏታል፡፡ መንግሥቱ ኃይለማርያም ጎርጎራን እና ደልጊን በጣና ዳር ያበቡ ከተሞች ለማድረግ ሕልማቸው ነበር፡፡ ያቺን ውብ የሆነች ውብ ሥፍራ ውብ አድርገው ማዬት ሕልማቸው ነበርና እየመጡ ያይዋት እንደነበርም ይነገራል፡፡ በዚያች ሥፍራ ጀልባዎች እና ታንኳዎች የሚያርፉባት ወደብም ይገኛል፡፡

ደልጊ ለብዙ ነገር የተመቸች እና የተስማማች ከተማ ናት፡፡ ውበትን እየሰጣት የሚኖረው ጣና ሐይቅ ለእርሷ ብዙ ነገሯ ነው፡፡ እርሷ ለመታዬት ብቻ ሳይሆን ለመሥራትም የተመቸች ሥፍራ ናት፡፡ በዚያዋ የሚመረተው ቅመማቅመም፣ በርበሬ እና ሌሎች ምርቶች ከጣና ጋር ተደማምረው፣ ከውበቷ ጋር አብረው ደልጊን ተመራጭና ተናፋቂ ያደርጓታል፡፡

የውበት ሠገነቷን ደልጊን ባያችኋት ጊዜ ውበትን ታደንቃላችሁ፡፡ ታሪክን፣ እሴትን፣ ሃይማኖትን ትማሩባታለችሁ፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በልጽጎ ሥራ ላይ የዋለ የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት መረጃ ሥርዓትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ጎብኝተዋል።
Next articleአንድ ነጥብ አምስት ቢልዮን ብር ያስመዘገቡ 126 ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ባለሐብትነት ተሸጋገሩ።