ለምርት ዘመን ከተገዛው የአፈር ማዳበሪያ 5 ሚሊዮን ኩንታሉ ሀገር ውስጥ ገብቷል።

126

ባሕር ዳር:ግንቦት 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ለ2015/16 የምርት ዘመን ከተገዛው 12 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ አምስት ሚሊዮን ኩንታሉ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ ከአዝመራ ወደቤተ ሙከራ የግብርና ሳይንስ ዓውደ ርዕይን አስመልክቶ እንደተናገሩት፤ ለ2015/16 የምርት ዘመን ከተፈጸመው 12 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ውስጥ አምስት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደሀገር ውስጥ ተጓጉዟል፡፡

ባለፈው የምርት ዘመን ተገዝቶ ሳይከፋፈል የቀረውን የአፈር ማዳበሪያ ከ2015/16 የምርት ዘመን የማዳበሪያ አቅርቦት ጋር በመደመር በዘንድሮው የምርት ዘመን 15 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ይቀርባል ብለዋል።

የአፈር ማዳበሪያው ለበልግ፣ ለመስኖና ለመኸር የግብርና ልማት ሥራ ጥቅም ላይ እንደሚውል ዶክተር ግርማ አስታውቀዋል።

ወደሀገር ውስጥ የገባው የአፈር ማዳበሪያ ለሕብረት ሥራ ማኅበራት መሰራጨቱን ዶክተር ግርማ ጠቁመዋል። የግብርና ግብዓት አቅርቦት ዋጋ ከአርሶ አደሩ አቅም ጋር የተመጣጠነ እንዲሆን መንግሥት ካለፈው ዓመት ጀምሮ የማዳበሪያ ድጎማ ማድረጉን ዶክተር ግርማ አስታውሰዋል።

መንግሥት በ2014/15 የምርት ዘመን ለቀረበው የአፈር ማዳበሪያ 21 ቢሊዮን ብር ድጎማ ማድረጉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

መንግሥት በግብርናው ዘርፍ ላይ እየታየ ያለውን መነቃቃትና ለውጥ ለማስቀጠል እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ዶክተር ግርማ አስረድተዋል።

የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦቱ የተሳለጠ እንዲሆን ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከሌሎች የፌዴራልና የክልል ተቋማት ጋር በትብብር የሚከናወኑ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦቱ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በመጠን ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ ማዳበሪያው በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ከማድረስ አኳያ ክፍተት መኖሩን ገልጸዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል። አርሶ አደሩ የሚቀርብለትን የተለያየ የግብርና ግብዓት በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት ማጠናከር እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል ሲል የዘገበው ኢፕድ ነው።

በተጨማሪም የአፈር ለምነትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የተፈጥሮ ማዳበሪያዎችን በስፋት ማዘጋጀትና መጠቀም እንደሚያስፈልግ ዶክተር ግርማ አስታውቀዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ተማሪ ከታተረ፣ መምህርም ከተጋ ጥሩ ውጤት እውን ይሆናል” መምህር ይበልጣል አዝዘው
Next articleበሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በልጽጎ ሥራ ላይ የዋለ የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት መረጃ ሥርዓትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ጎብኝተዋል።