“ተማሪ ከታተረ፣ መምህርም ከተጋ ጥሩ ውጤት እውን ይሆናል” መምህር ይበልጣል አዝዘው

212

👉 በ2015 የትምህርት ዘመን 50 እና ከዚያ በላይ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ብቻ ናቸው ወደ ዘጠነኛ ክፍል የሚያልፉት።

ባሕር ዳር:ግንቦት 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ተማሪ አሰፋ ይበልጣል በምሥራቅ ጎጃም ዞን ቢቡኝ ወረዳ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነው። ከገጠር አካባቢ ወደ ድጎ ጽዮን ከተማ በመምጣት ልዩ የማጠናከሪያ ትምህርት ሲወስድ ነው ያገኘነው። የ2015 ዓ.ም የስምንተኛ ክፍል ፈተና ከወትሮው ይለያል። ወደ 9ኛ ክፍል ለማለፍ 50 እና ከዚያ በላይ ውጤት ማስመዝገብ ግድ ነው። የተማሪ አሰፋ ህልም ግን 50 ማምጣት ብቻ አይደለም። ከ95 በላይ በማስመዝገብ፣ በክልሉ ተወዳዳሪ ኾኖ ወደ አዳሪ ትምህርት ቤት መግባት፣ ከዚያም የሀገር አቀፉን የ12 ክፍል ፈተና ቁንጮ ውጤት በማምጣት በክብር ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት ነው የተማሪው ህልም። “የታተረ ተማሪ ሀገር አቀፍ ተወዳዳሪ፣ ብሎም አሸናፊ መኾኑ አይቀርም፤ ራሱ ኮርቶ ቤተሰብ እና አካባቢውንም ያስመሰግናል” ብሏል ተማሪው

የተማሪ አሰፋን ህልም የሚጋሩ፣ አብረውትም የሚታትሩ ብዙ ናቸው። ከወረዳው ሁሉም ትምህርት ቤቶች በቀለም ውድድር አሸናፊ በመኾን የተመረጡ ባለምጡቅ አዕምሮ ተማሪዎች በድጎ ጽዮን ከተማ ተሰባስበው የተመቻቸላቸውን ልዩ የማጠናከሪያ ትምህርት እየወሰዱ ነው። በወረዳው ያሉ ሁሉም የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግቡ በትኩረት እየተሠራ ነው። ለነተማሪ አሰፋ የሚሰጠው ልዩ የማጠናከሪያ ትምህርት ደግሞ በክልሉ ወደሚገኙ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በተወዳዳሪነት እንዲገቡ የሚያስችል ነው።

ከየትምህርት ቤቱ ከተመረጡ ጎበዝ ተማሪዎች ጋር መማሩ እርስ በእርስ እየተረዳዱ ለማጥናት ዕድል እንደፈጠረለት የሚናገረው ተማሪ አሰፋ ልዩ የማጠናከሪያ ትምህርቱ በተመረጡ ታታሪ መምህራን የሚሰጥ በመኾኑ ለተወዳዳሪነት እና አሸናፊነት እንደሚያዘጋጃቸው ገልጿል፡፡

ይህንን ልዩ የማጠናከሪያ ትምህርት ከሚሰጡት መምህራን መካከል መምህር ይበልጣል አዝዘው አንዱ ናቸው። እርሳቸው የመሰናዶ መምህር ቢኾኑም ትርፍ ጊዜያቸውን አሟጠው በመጠቀም ወደ ስምንተኛ ክፍል ወርደው የማጠናከሪያ ትምህርቱን እየሰጡ ነው። “ተማሪ ከታተረ፣ መምህሩ ከተጋ ጥሩ ውጤት እውን ይሆናል” ይላሉ።

ልዩ የማጠናከሪያ ትምህርቱ እሁድ እና ቅዳሜን ጨምሮ በሁሉም ቀናት እንደሚሰጥ መምህር ይበልጣል ተናግረዋል። ተማሪዎች የሚሰጠውን የ8ኛ ክፍል ፈተና በጥሩ ውጤት አጠናቅቀው ወደ ተሻለ ትምህርት ቤት እንዲቀጥሉ በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑም ገልጸዋል። በልዩ የማጠናከሪያ ትምህርቱ ሁሉም የትምህርት አይነቶች እንደሚሰጡም ተናግረዋል።

የቢቡኝ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ተወካይ ኃላፊ አቶ አዲስ ጌትነት በርካታ ተማሪዎች ተወዳዳሪ ውጤት አምጥተው ወደ አዳሪ ትምህርት ቤቶች እንዲቀላቀሉ በወረዳ ደረጃ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል። በቢቡኝ ወረዳ በ2015 ዓ.ም 1 ሽህ 681 ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ፈተና እንደሚወስዱ ገልጸዋል።

ሁሉም ተማሪዎች የሚሰጣቸውን ፈተና በራሳቸው አቅም ሰርተው ጥሩ ውጤት በማስመዝገብ ወደ ቀጣይ ክፍል መዘዋወር እንዲችሉ ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ ስለመኾኑም ገልጸዋል። በወረዳው የሚገኙ የተሻሉ መምህራን ተመርጠው ድጋፋን እንዲሰጡ መመቻቸቱንም ተናግረዋል።

ተማሪዎች የፈተና ኩረጃን በመጥላት የራሳቸውን ውጤት ብቻ እንዲያገኙ ከወዲሁ የሥነ ልቦና ዝግጅት እየተደረገ ስለመኾኑም አቶ አዲስ ገልጸዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ አቶ ጌታሁን ፈንቴ በ2015 የትምህርት ዘመን የ8ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግቡ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል። በዚህ ዓመት የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ወደ ቀጣዩ ክፍል ለማለፍ 50 እና ከዚያ በላይ ውጤት ማስመዝገብ ግዴታ መኾኑን ገልጸዋል።

በርካታ የ8ኛ ክፍል ተማሪዎችን ወደ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ሊያስገባ የሚችል ውጤት እንዲያስመዘግቡ ለማስቻል ዞኑ በትኩረት እየሠራ ስለመኾኑም አቶ ጌታሁን ተናግረዋል። ልዩ ተሰጥዖ ያላቸው ተማሪዎች በውድድር ተመርጠው ከተለዩ በኃላ በየወረዳው ወደ ተዘጋጀላቸው ማዕከል እንዲሰባሰቡ ተደርጓል። እነዚህ ተማሪዎች በተመረጡ መምህራን ለፈተና የሚያዘጋጃቸውን ትምህርት እየወሰዱ ነው። በትርፍ ጊዜያቸው ለሚያስተምሩት መምህራንም የማበረታቻ ክፍያ የተዘጋጀ ስለመኾኑ መምሪያ ኀላፊው ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ምሳሌ የሚኾን ተቋም ነው” አቶ ቢያዝን እንኳኾነ
Next articleለምርት ዘመን ከተገዛው የአፈር ማዳበሪያ 5 ሚሊዮን ኩንታሉ ሀገር ውስጥ ገብቷል።