“በቦሩ ሜዳ ሆስፒታል በተደረገልን ነጻ የዓይን ቀዶ ሕክምና የዐይን ብርሃናችን በመመለሱ ተደስተናል” ታካሚዎች

51

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በተደረገላቸው የዓይን ቀዶ ሕክምና የአይን ብርሃናቸው በመመለሱ መደሰታቸውን በቦሩ ሜዳ ሆስፒታል የዓይን ሞራ ግርዶሽ ሕክምና ያገኙ ታካሚዎች ገለፁ።

ሆስፒታሉ በበኩሉ በዓይን ሞራ ግርዶሽ ለታመሙ ለ1 ሺህ ሰዎች ነጻ የዓይን ቀዶ ሕክምና መስጠቱን አስታውቋል።

ነጻ የሕክምና አገልግሎት ካገኙት መካከል በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ አስናቀች ኡመር ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ሁለቱንም የዓይን ብርሃናቸውን ካጡ ሁለት ዓመታት ተቆጥሯል።

በእነዚህ ዓመታት የከፋ ጊዜ ማሳለፋቸውን ያስታወሱት ነዋሪዋ፣ “እየተሰቃየሁ ከመሞት ውጪ የዓይን ብርሃኔ ይመለሳል የሚል ተስፋ አልንበረኝም” ብለዋል።

“በልጆቼ እየተመራሁ መጥቼ ባገኘሁት ነጻ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ሕክምና የሁለቱም አይኖቼ ሙሉ ብርሃን ተመልሷል፤ አሁን ያለደጋፊ ቁሜ መሄድ በመጀመሬ ዳግም የተወለድኩ ያህል ደስታ ተሰምቶኛል” ብለዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን አልቡኮ ወረዳ ነዋሪ አቶ ደምሴ ጀማል በበኩላቸው “በሕክምናው የሁለቱም አይኖቼ ብርሃን ተመልሶ ዳግም ማየት በመጀመሬ ደስታዬ ወደር የለውም” ሲሉ ገልጸዋል።

ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ በሰው እየተመሩ በችግር ማሳለፋቸውን አስታውሰው፣ አሁን በተደረገላቸው ሕክምና ብርሃናቸው መመለሱን ገልጸዋል።

በሹፍርና ሥራ ይተዳደሩ እንደነበርና ዓይኖቻቸው ማየት ሲያቆሙ ከሥራ ውጪ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪው አቶ አሊ መሃመድ ናቸው።

“በአሁኑ ወቅት የዓይን ብርሃኔ ተመልሶ ማየት በመቻሌ ተደስቻለሁ፣ ሰው ማስቸገርም ስላቆምኩ ብርሀኔን ለመለሱልኝ አመሰግናለሁ” ብለዋል።

በቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል የዓይን ሕክምና ክፍል ሃላፊ አቶ እንዳልክ ያረጋል በበኩላቸው፤ ከሚያዚያ 30 እስከ ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም በዓይን ሞራ ግርዶሽ ለታመሙ 1 ሺህ ሰዎች ነጻ የዓይን ቀዶ ሕክምና በዘመቻ ተሰጥቷል።

የዓይን ሞራ ግርዶሽ በአብዛኛው ከዕድሜ ጋር ተያይዞ የሚከሰት የጤና ችግር መሆኑን ገልጸው፣ ለዓይነ ስውርንነት ከሚያጋልጡ ምክንያቶች መካከል 51 በመቶውን ድርሻ እንደሚይዝም አስረድተዋል።

የዓይን ሞራ ግርዶሽ በወቅቱ ካልታከመ የዓይን ብርሃንን ሙሉ በሙሉ እስከማሳጣት እንደሚደርስም ተናግረዋል።

የቀዶ ሕክምና ዘመቻው ዓላማ በሆስፒታል ለመታከም እድሉን ያላገኙ ወገኖችን ማገዝ መሆኑን ጠቁመው፣ በህክምና ዘመቻው 1 ሺህ ሰዎች የዓይን ብርሃናቸው መመለሱን ተናግረዋል።

የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ተበጀ በበኩላቸው ሆስፒታሉ በተለያየ ዘመቻ በዓይን ሞራ ግርዶሽ ለሚሰቃዩ ሰዎች ነጻ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል።

በደሴ ከተማ አስተዳደር የሚገኘው የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ባለፉት አራት ዓመታት ከ10 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የዓይን ሕክምና አገልግሎት መስጠቱን ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶችን በዘመነና በተደራጀ  መንገድ ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ።
Next articleባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባለፉት 60 ዓመታት የሚሠሩ እጆችን ያፈራ ተቋም እንደኾነ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ፍሬው ተገኝ(ዶ.ር) ገለጹ።