
ባሕር ዳር: ግንቦት 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አዲስ ህይወት ሪሃብሊቴሽን እና ሪኢንተግሬሽን አሶሴሽን (አህራ) የተባለ ድርጅት ከክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ጋር በመተባበር ግጭቶችን አስቀድሞ መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
“አህራ” በአማራ ክልል በስድስት ዞኖች የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።
የድርጅቱ ፕሮግራም አስተባባሪ አሕመድ ሙሐመድ እንደገለጹት ድርጅቱ በሰሜን ወሎና በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በአብሮነት እሴትና በሀገር በቀል የሽምግልና ሥርዓት ላይ እየሠራ ነው። በዚህም በቅርቡ በቆቦ ተከሰቶ የነበረው ግጭት በሀገር በቀል ሽምግልና መፈታቱን ለአብነት አንስተዋል።
ድርጅቱ በቀጣይ ከክልሉ ውጭ በአጎራባች ክልሎች እንደሚሠራም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ኮማንደር መንገሻ አውራሪስ እንዳሉት በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረውን የፀጥታ ችግር በሀገር በቀል የሽምግልና ሥርዓት መፍታት ተችሏል።
ከዚህ በፊትም ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተሠራው ሥራ በሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አካባቢዎች ተፈጠሮ የነበረው የፀጥታ ችግር መፈታቱን አውስተዋል።
ከእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተሠራው ሥራም በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደርና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዋሳኝ አካባቢ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር መፈታቱን ተናግረዋል።
የሚፈጠሩ ግጭቶችን ዘላቂ በኾነ መንገድ ለመፍታት ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎችን በዘመነ መንገድ ማስቀጠል እንደሚገባም ነው ያስረዱት። ለዚህ ደግሞ ግብረሰናይ ድርጅቶች እና ምሁራን ሊያግዙ እንደሚገባ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
