“ለአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች መፍትሔው ሕዝባዊ መሠረት ያለው ጠንካራ መዋቅራዊ ዴሞክራሲያዊ ትግል ነው” አወል አሊ የፖለቲካ ሳይንስና የፍልስፍና መምህር

64

ባሕርዳር : ግንቦት 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ የሚባሉ ጥያቄዎች ያሉበት ሕዝብ ነው፡፡ ጥያቄዎቹ ደግሞ በሚወዳት ሀገሩ በእኩልነት እና በአንድነት መኖርን መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡

ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና የፍልስፍና መምህሩ አወል አሊ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በግልጽ የሚነሱ መኾናቸውን ይናገራሉ፡፡ ጥያቄዎቹ በሕዝቡ፣ በምሁራን፣ በሚዲያ ባለሙያዎች እና በሌሎች አካላት የሚነሱ ግልጽና ዓመታትን የወሰዱ መኾናቸው ነው የተናገሩት፡፡

የአማራ ሕዝብ ካለፉት ሠላሳና አርባ ዓመታት ጀምሮ በተለያዩ ፖለቲካዊ ጫናዎች ፍርደኛ ኾኖ የሚኖር ነው ያሉት መምህሩ በአለፉት ዓመታት የተመሠረቱ የፖለቲካ ሥርዓቶች የአማራ ሕዝብ እንደጨቋኝ ተቆጥሮ  አያሌ ዋጋዎችን መክፈሉን ገልጸዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የእኩልነትና የመብት ጥያቄዎች እንጂ ለእኔ ብቻ ሁሉን የሚል አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሬ ተጠቃሚ ኾኜ፣ መብቴ ተረጋግጦልኝ በእኩልነት ልኑር የሚል ሕዝብ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በሀገረ መንግሥት ግንባታ ታላቅ ሚና ያለው ሕዝብ ነው ያሉት ምሁሩ ከጊዜ በኋላ ፊት የተዞረበት፣ ለሠራው መልካም ሥራ በሴራ ግፍ የተቀበለ ሕዝብ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ መገለል የደረሰበት ሕዝብ መኮኑንም ነው የገለጹት፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ሰላማዊና እና ዴሞክራሲያዊ የመፍትሔ አማራጮችን መጠቀም ይገባልም ነው ያሉት።

የአማራ ሕዝብ ጥያዌች እንዴት መፍትሔ ያግኙ? የሚለውን ምላሽ ሲሰጡ ጥያቄዎችን ለመመለስ ሕዝባዊ መሠረት ያለው ዴሞክራሲያዊ ትግል ያስፈልጋል፣ የአማራ ሕዝብን ጥያቄዎች ይዘናል ብለው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች የእውነት የሕዝብ ጥያቄዎችን ይዘዋልን? የሚለውን መፈተሸ ይገባል፣ የሕዝብን ጥያቄ ካልያዙ በትክክል የሕዝብ ጥያቄ እንዲይዙ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ሚዲያዎች፣ ምሁራን፣ በውጭ የሚኖሩ የአማራ ተዋላጆች የሕዝብን ጥያቄ ማቅረብ እና ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ በኾነ መንገድ  መታገል ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

ለሕዝብ ጥያቄ የሚሠራ የተቀናጀ፣ ጠንካራና ሕዝባዊ መሠረት ያለው ሰላማዊ ትግል ማድረግ ለአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች መመለሻ መንገድ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡  ትግሉ መሥመርና አቅጣጫ፣ የጸና አቋም እና አንድነት ካለው የማይመለስ ጥያቄ የለም ብለዋል፡፡

ሕዝቡ የደራጀ መሆን አለበት ያሉት ምሁሩ ምሁራን ጥናት በማድረግና የመፍትሔ አቅጣጫ በማስቀመጥ፣ ሚዲያ እውነትን በማውጣት እና ሌሎችም በየዘርፋቸው አወንታዊ ሚና ከተጫወቱ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎቹ ይፈታሉ፣ የአማራን ሕዝብ የሚጎዳ ሥርዓትም አይኖርም ነው ያሉት፡፡

የአማራ ሕዝብ ሲደራጅ፣ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ እና ለማልማት መሥራት ያስፈልጋል፤ ይህን የሚረዳ ሕዝብና መሪም መፈጠር አለበት ነው ያሉት፡፡ ሕዝብና መሪዎቹ አንድ ከኾኑ የማይፈታ ችግር እንደማይኖሩም ገልጸዋል፡፡ የሕዝብና የመሪዎች አንድነት በመተማመን ላይ የኾነና በፈተናዎች የሚጸና መኾን እንደሚገባውም አስታውቀዋል፡፡

ፈተናዎችን ተቋቁሞ የአማራን ሕዝብ ፍላጎቶች ማሟላት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ሌላውን ልብለጥ የሚል አመለካከት የሌለው፣ ትክክለኛ ውክልና ላግኝ፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ይኑረኝ፣ በሀገሬ በሰላም ሰርቼ ልደግ የሚል ነውም ብለዋል፡፡

ለዓመታት የተዘራው የሐሰት ትርክት አንድነትን እየተፈታተነ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ስለመጪው ትውልድ የሚያስብ ውይይት እና ምክክር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ ዘመኑን የዋጀ ጠንካራ፣ መዋቅራዊ፣ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ትግል ማድረግ ጥያቄዎችን መፍትሔ ለመስጠት፣ የሕዝብን ችግሮች ለመቅረፍ እና ፈተናዎችን ለመሻገር እንደሚያስችልም አስገንዝበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኢንጅነር ተረፈ ራሥ ወርቅ የተሰየመ የሳይንስና ፈጠራ ውጤት የሽልማት ሥነ ሥርዓት በሳይንስ ሙዚየም እየተከናወነ ነው።
Next articleሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶችን በዘመነና በተደራጀ  መንገድ ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ።