
ባሕርዳር : ግንቦት 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በሥነ ምግባርና ግብረ ገብነት ግንባታ ዙሪያ ያሠለጠናቸውን የባሕርዳር ከተማ ጣና ሐይቅ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።
ሥልጠናው ከየካቲት 30/2015 እስከ ሚያዚያ 3/2015 “በላቀ የሥነ ምግባር ግንባታ ከሙስና እና ብልሹ አሠራር የጸዳ ትውልድ እንፍጠር” በሚል መሪ ሃሳብ ሲሰጥ ቆይቷል።
በአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ማሩ ቸኮል የሥነ ምግባር ግንባታ ጊዜ የሚፈጅ እና በትኩረት ሊሠራበት የሚገባ ነው ብለዋል። በክልሉ በሁሉም የመንግሥት እና የግል ትምህርት ቤቶች የሥነ ምግባር ክበብ ተቋቁሞ ተማሪዎችን በግብረገብነት ለመቅረጽ ኮሚሽኑ ከትምህርት ቢሮ ጋር እየሠራ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
ምክትል ኮሚሽነር ማሩ እንደ ሀገር የተበላሹ ነገሮችን ለማረም ትምህርት ቤት ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ኮሚሽኑ ከትምህርት ቤቶች ጋር በመተባበር በቀጣይነት እንደሚሠራም ተገልጿል።
በአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የሥነ ምግባርና ግብረገብነት ሥልጠና ባለሙያ አቶ ዘላለም ንጉሤ “ስግብግብነት ልኩን እየሳተ፣ የግል ተጠቃሚነት ብቻ እየቀደመ” ነው ብለዋል። ይህ አካሄድ ለሀገር ስለማይጠቅም እና መታረም ስላለበት የተሻለ ሥነ ምግባር እና ግብረገብነት ያስፈልጋል ብለዋል። በተለይም ወጣቶች በግብረገብነት እንዲያድጉ የክልሉ ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ሥልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ አቶ ዘላለም ገልጸዋል።
ሥልጠና የወሰዱ 25 ሴቶች እና አምስት ወንዶች በድምሩ 30 ተማሪዎች ዛሬ ተመርቀዋል። ሠልጠኝ ተማሪዎች ያገኙትን ዕውቀት የሚለካ ፈተና ወስደው እንደተመረቁም ተናግረዋል።
ዛሬ የተመረቁት ተማሪዎች ሁለተኛ ዙር ሰልጣኞች ናቸው። ኮሚሽኑ በመጀመሪያው ዙር ሥልጠና የሰጣቸው 32 ተማሪዎች “ኢትዮጵያዊ የሥነ ምግባር እና የግብረ ገብ ማኅበር” መስርተው በክልሉ መንግሥት የዕውቅና ፈቃድ አግኝተው በመንቀሳቀስ ላይ መኾናቸውንም አቶ ዘላለም ገልጸዋል።
ዛሬ ከተመረቁት መካከል በጣና ሐይቅ መሰናዶ ትምህርት ቤት የ12 ኛ ክፍል ተማሪዋ ማስተዋል አግማሴ አንዷ ናት። “ጥሩ ሥነ ምግባር ቤተሰብ ከማክበር ይጀምራል” ያለችው ተማሪዋ ያገኘችው ሥልጠና ከቤተሰብ ጀምሮ ከሁሉም ማኅበረሰብ ጋር ሊኖራት የሚችለውን መስተጋብር የሚያሳምር መኾኑን ገልጻለች።
ሥልጠናው ተማሪዎች በቤተሰብ ውስጥ እና በትምህርት ቤት ምን አይነት ግብረ ገብነት መያዝ እንደሚገባቸው ግንዛቤ የሚያስጨብጥ እንደነበር ተማሪ ማስተዋል ተናግራለች።
ሌላዋ የሥልጠናው ተካፋይ ተማሪ ፈንታነሽ ደባሽ “ከተሰጠው ሥልጠና ለወደፊት ምን አይነት ሥነ ምግባር ይዤ ማደግ እንዳለብኝ ግንዛቤ አግኝቸበታለሁ” ብላለች። ልጆች የወላጆቻቸውን ሃሳብ ማክበር እና በማኅበረሰቡ ውስጥ አላስፈላጊ የኾኑ ድርጊቶችን በመጸየፍ ማደግ እንዳለባቸውም መክራለች።
የ11ኛ ክፍል ሰልጣኝ ተማሪው በቃሉ ጌታቸው በሀገሪቱ ላይ የሚስተዋለውን ብልሹ አሠራር ለመቅረፍ የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት ወደ ሥልጠናው መግባቱን ገልጿል። ሀገር እና ሕዝብን የሚጎዱ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ከምን አገባኝ ባይነት ስሜት ወጥተን በጋራ መታገል ያስፈልጋልም ብሏል።
“ጥሩ ሥነ ምግባር ከቤተሰብ እና ከትምህርት ቤት ይጀምራል” ያለው ተማሪው ሙስናን የሚጠላ ዜጋ ለማፍራት ወላጆች እና መምህራን ትልቅ ኀላፊነት አለባቸው ብሏል። ወጣቶችም ነገ የሚረከቧትን ሀገር በሥነ ምግባር ለመምራት ከወዲሁ ራሳቸውን ማነፅ አለባቸው ሲል መልዕክት አስተላልፏል።
የጣና ሐይቅ መሰናዶ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ሙጨ ባዝዘው በትምህርት ቤቱ ውስጥ የሚሰጠው የግብረ ገብነት ሥልጠና ለተማሪዎች ሥነ ምግባር መሻሻል አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል። “የተማሪዎች የትምህርት ውጤት ከሥነ ምግባራቸው ጋር ግንኙነት አለው” ያሉት ርእሰ መምህሩ ጥሩ ሥነ ምግባር ያለው ተማሪ በትምህርቱም ውጤታማ ይኾናል ብለዋል።
በትምህርት ቤቱ ጠንካራ የግብረ ገብነት ሥልጠናዎች መሰጠት ከተጀመረ ወዲህ ይስተዋል የነበረው የተማሪዎች የሥነ ምግባር ግድፈት እየተስተካከለ ስለመኾኑም ርእሰ መምህሩ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
