“የመካነ-ኢየሱስ/እስቴ-ስማዳ 50 ነጥብ 5 ኪ.ሜ አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ወደ መጠናቀቅ ተቃርቧል” የኢትዮጵያ መንገዶች ባልስልጣን

214

ባሕር ዳር: ግንቦት 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን የመካነ-ኢየሱስ/እስቴ-ስማዳ 50 ነጥብ 5 ኪ.ሜ አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ወደ መጠናቀቅ መቃረቡን የኢትዮጵያ መንገዶች ባልስልጣን አስታውቋል። እንደ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ መረጃ፣ አሁን ላይ ከአጠቃላይ የግንባታ ሥራው 86 በመቶው ተከናውኗል። ቀሪ ሥራዎቹን በሚቀጥሉት አምስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሠራ ነው።

ከጠቅላላው የመንገዱ ክፍል 47 ኪሎ ሜትሩን አስፋልት ማልበስ ተችሏል። በተጨማሪም የአፈር ቆረጣ እና ሙሌት፣ የሰብቤዝ እና ቤዝኮርስ፣ የሾልደር፣ የውኃ መፋሰሻ፣ የድልድይ እንዲሁም የማጠናቀቂያ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡

ግንባታውን ዓለም አቀፉ ‘ቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ’ እያከናወነ ይገኛል።

ለግንባታው ከ1 ቢሊዮን 925 ሚሊዮን 451 ሺህ በላይ በፌዴራል መንግሥት ነው የተሸፈነው።

‘ፕሮሚናንት ኢንጅነሪንግ ሶሉሽንስ’ ግንባታውን የመቆጣጠር እና የማማከር ሥራ እየሠራ ይገኛል።

አካባቢው ካለው በርካታ ሀገራዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አንፃር በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ ነው እየተገነባ የሚገኘው፡፡

በፕሮጀክቱ የከተማ ክልል ላይ ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ችግር በግንባታ ሥራው ላይ እክል ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከወረዳ የመስተዳድር አካላት ጋር በመቀናጀት ችግሩን መፈታት ተችሏል፡፡

ከዚህም ባለፈ የአካባቢው አስቸጋሪ የመልካ-ምድራዊ አቀማመጥ እንዲሁም የግንባታ ዕቃዎች የግብዓት ዕጥረት እና የዋጋ መናር በግንባታው ወቅት የገጠሙ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡

የእስቴ-ስማዳ አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ከአዲስ አበባ 657 ኪ.ሜ ርቀት እስቴ ከተማ ላይ ጀምሮ ወገዳ ከተማ ድረስ ይዘልቃል፡፡

ፕሮጀክቱ ዕውን ሲሆን በሥፍራው የሚገኙትን ትንንሽ መንደሮች ደረጃውን በጠበቀ መንገድ በማገናኘት ወደ ከተማ የሚያድጉበትን ምቹ ዕድል ይፈጥራል፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩን በማሳለጥም የተለያዩ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮችን ያጠናክራል፡፡

በአካባቢው በስፋት የሚመረቱትን ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ሽንብራ፣ ኑግ፣ ባቄላ፣ ጓያ፣ ድንች እና መሰል የግብርና ምርቶች ገበያ በፍጥነት እና በጥራት ማድረስ ያስችላል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጥሩ ሀገር ለመገንባት ቅድሚያ ጥሩ ቤተሰብ መገንባት ላይ መሥራት ይኖርብናል” የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናትና ማኀበራዊ ጉዳይ ቢሮ
Next article“የልዩ ኀይል ሪፎርም የተተገበረው በክልል የተከፋፈለ ልዩ ኀይል ሳይኾን ሰብሰብ ያለና ጠንካራ ተልዕኮውን መወጣት የሚችል የጸጥታ ኀይል ለመገንባት ነው” የአማራ ክልል ሰላምና ደህንነት ቢሮ ኀላፊ