
ባሕር ዳር: ግንቦት 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ)ዘንድሮ በዓለም ለ30ኛ ጊዜ የሚያከብረውን ዓለም አቀፉ የቤተሰብ ቀን፣ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ እያከበረች ነው።
ቤተሰብ ለሀገር ግንባታና ለትውልድ ሰብእና ግንባታ ያለውን ሚና በአግባቡ እንዲወጣ ታላሚ ተደርጎ ቀኑ በተለያዩ የመወያያ አጀንዳዎች ይከበራል።
የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናትና ማኀበራዊ ጉዳይ ቢሮም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበረውን የቤተሰብ ቀን “የቤተሰብ ሚና ለትውልድ ሰብእና”በሚል መሪ መልእክት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች አክብሮታል።
በፕሮግራሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናትና ማኀበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ እንደተናገሩት የቤተሰብ ተቋም በትውልድ ሰብእና ግንባታ ላይ ሚናውን እንዲወጣ ሀገራዊ ግብ ተይዞ እየተሠራ ነው።
“ቤተሰብ ላይ መሥራት ሀገር ላይ መሥራት ነው” የሚሉት ኀላፊዋ ጥሩ ቤተሰብ መገንባት የሚችል ጥሩ ጎረቤት፣ ጥሩ መንደር፣ ጥሩ ሀገር ለመገንባት የሚያስችል ሰብእናን የተላበሰ ልጆችን ማፍራት የሚችል ነው ብለዋል።
የቤተሰብን መሠረት ማስያዝ እንደ ሀገር በማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ሁሉ መሠረት ማስያዝ እንደኾነም ሊታወቅ ይገበዋል ነው ያሉት።
እንደ ሀገር የሚፈጠሩ ስንጥቆች፣ በነጠፈ ሰብእና የሚከሰቱ ችግሮች ሁሉ የቤተሰብ መሰረት ብልሽት ውጤት ስለመኾኑም ነው የተናገሩት።
ለዚህ ለሀገር ግንባታና ለትውልድ ሰብእና መሠረት ከኾነው ቤተሰብ ግንባታ ላይ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
ለሀገር ኩራት የሚኾኑ፣የነገ ሀገር ተረካቢ ልጆች በመልካም ሰብእና ተቀርጸው እንዲያድጉ መሠረቱ ቤተሰብ ነው ተብሏል፡፡ ቤተሰብ ትልቅ ማኀበራዊ ተቋም ስለመኾኑም በመድረኩ ተነስቷል።
በትውልድ የሚገነቡ መልካም ሰብእናዎች፣ መረዳዳት፣ ግብረ ገብነት፣ መዋደድ፣ መቻቻል፣ አብሮነት፣ ሰላማዊ ግንኙነት፣ ለሀገር ምሰሶ የኾኑ መልካም እሴቶች ሁሉ ተጠናክረው የሚቀጥሉት ቤተሰብ ሚናውን ሲወጣ ነው ተብሏል።
በመድረኩ”ቤተሰብ የሀገር መሠረት ነው ሲባል ምን ማለት ነው፣የቤተሰብ ምንነትና ጠንካራ ቤተሰብ ለመገንባት የሚያግዙ ጉዳዮች” ላይ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
በቤተሰብ ደህንነት፣በጋብቻና ፍች ላይ የሚሠራው “ሰላም የበጎ አድራጎት ድርጅት” በመድረኩ ተሞክሮውን አቅርቧል።
በመድረኩ በክልሉ ከዘጠኙ ሜትሮፖሊታንት ከተሞች የመጡ የሴቶች ሕጻናትና ማኀበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊዎች እና ቢሮ ኀላፊዎች ተሳታፊዎች ናቸው ተብሏል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
