
ባሕር ዳር: ግንቦት 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገርን ክብር እና ሉዓላዊነት፤ የሕዝብ ደኅንነት እና ነፃነት ከሚያስከብሩ ባለአደራዎች መካከል ወታደር ቀዳሚው ነው፡፡ ውትድርና አካልን እና ሕይዎትን ገብሮ ሀገር እና ሕዝብ የማስቀጠልን ተቀዳሚ ተልዕኮ ያነገበ አኩሪ ሙያ ነው፡፡ ወታደር ማለት ተራራ ወጥቶ ቁልቁለት ወርዶ፤ የኮዳ ውኃ ተጋርቶ የወደቀ ጓደኛውን ተራምዶ ራስን ስለሀገር እና ትውልድ አሳልፎ የመስጠት ጸጋን የተላበሰ አደራ ነው፡፡
ረጂም የነፃነት ዘመን እና ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ እንደ ጅረት በሚፈሰው፤ እንደ ሀረግ በሚመዘዘው የትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ብዙ ያልተዘመረለት የነፃነት ድርሳን ባለቤት ናት፡፡ ሀገሪቱ በየዘመኑ ለገጠሟት ፈተናዎች ሁሉ አኩሪ እና አንጸባራቂ ድሎችን እንደ ሸማ ያለበሷት ክንደ ብርቱ ልጆችን አፍርታለች፡፡ ኢትዮጵያ ፈታኞቿን አምበርክከው፤ ጠላቶቿን አዝረክርከው የማይታመን ተጋድሎዎችን የፈጸሙ ልጆቿ የእጅ ሥራ ውጤት ናት፡፡
ዘመኑ በሚፈቅደው እና ሁኔታው በሚያስገድደው መልኩ አደረጃጀቱን እያሻሻለ የመጣው የውትድርና ሙያ ከጥንት እስከ ዛሬ ብዙ ለውጦችን አሳይቷል፡፡ እንደየ ግዳጁ፣ እንደየ አደረጃጀቱ፣ እንደየ ተልዕኮ እና እንደየ ብቃቱ የተለያየ መልክ የነበረው የኢትዮጵያ ወታደር ምንጊዜም ዓላማው ሀገርን ማስቀጠል እና የሕዝብን ሕልውና መጠበቅ ነበር፡፡ የቀደመውን ትተን የቅርብ የቅርቡን ብናነሳ እንኳን የኢትዮጵያ ወታደር ውስጣዊ እና ውጫዊ ጫናዎችን መክቶ ሀገር ስለማስቀጠሉ እልፍ ምስክሮች አሉት፡፡
በቅርቡ ኢትዮጵያ የሕልውና አደጋ በገጠማት ወቅት ፈጥነው ደርሰው የበርካቶችን ሕይዎት ከታደጉ እና የሀገርን ሕልውና ካጸኑ የውትድርና ሙያ ዘርፍ ተጋሪዎች መካከል የቀድሞው የአማራ ልዩ ኀይል አባላት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የአማራ ልዩ ኀይል ውስጣዊ ልዩነቶችን በሠላም እና በውይይት መፍታት ተስኗቸው ሀገር እና ሕዝብን ለሕልውና አደጋ ያጋለጡ ኀይሎችን ጥቃት መክቶ ያቆመ የባለደማቅ ታሪክ ባለቤት ነው፡፡ የአማራ ልዩ ኀይል በተደጋጋሚ የተቃጡ ጥቃቶችን እና ትንኮሳዎችን ከአጋሮቹ ጋር ኾኖ በመመከት ትውልድ የማይዘነጋው አበርክቶ አለው፡፡
የአማራ ልዩ ኀይል አባላት ኢትዮጵያ ለዓመታት ከዘለቀው የሰሜኑ ጦርነት ወጥታ የሠላም ሥምምነት ላይ እንድትደርስ የማይቻለውን ሁሉ ችለው ያሳለፉ ክንደ ብርቱዎች ናቸው፡፡ ደም አፋሳሹ ጦርነት በሠላም እንዲቋጭ ምክንያት ከኾኑት ኀይሎች መካከል የአማራ ልዩ ኀይል ተጋድሎ አንዱ ነው፡፡ የማይካድ ሀቅ ቢኖር የሠላም ሥምምነቱ የአማራ ልዩ ኀይል አንዱ የተጋድሎ ውጤት ጭምር መኾኑ ነው፡፡
ትናንት የሕልውና ጦርነት ውስጥ የነበረችው ኢትዮጵያ ዛሬ አንጻራዊ ሠላም ላይ ናት፡፡ የሠላም ባለቤት የኾነውን የአማራ ልዩ ኀይል አባላት በላቀ ደረጃ መልሶ ማደራጀት ተጀምሯል፡፡ “ሀገር ስትፈልገን ሁሌም ዝግጁ ነን” ያሉ የልዩ ኀይል አባላቱም ከቀረቡላቸው አማራጮች መካከል በየፈለጓቸው የጸጥታ ተቋማት ውስጥ እየገቡ ነው፡፡
ለዘመናት ያካበቱትን የውትድርና ሙያ ክህሎት እና ዕውቀት በመጠቀም የተሰጣቸውን ግዳጅ እና ኅላፊነት በብቃት እንደሚወጡም ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡
ረዳት ኮሚሽነር ሞላ ብርሃኔ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ሀገራቸውን እና ሕዝቡን በወታደርነት ሙያ አገልግለዋል፡፡ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እስከ አማራ ልዩ ኀይል ባገለገሉባቸው ዓመታት ስለሕዝብ እና ሀገር ሲባል ብዙ ውጣ ውረዶችን፤ አያሌ ፈተናዎችን አሳልፏል፡፡ ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ የሕልውና አደጋ ውስጥ በነበረችባቸው ወቅት ከዋሊያ ክፍለ ጦር እስከ ጋሻ ክፍለ ጦር ተዋግተው አዋግተዋል፡፡ ያንን ወቅት “ለአማራ ሕዝብ ሕልውና የተከፈለ አኩሪ መስዋእትነት ነበር” ብለዋል፡፡
“ወታደር ሳይንሳዊ ሙያ ነው” የሚለው ረዳት ኮሚሽነር በየትኛውም አደረጃጀት ውስጥ ኾኖ ሕዝብን ማገልገል እና ግዳጅ መቀበል ደግሞ የሙያው የተለየ ተሰጥኦ ተደርጎ ይወሰዳል ይላሉ፡፡ “ትናንት ኢትዮጵያ እና የአማራ ሕዝብ የሕልውና አደጋ ሲደቀንባቸው የአማራ ልዩ ኀይልን እየመራሁ ከጠለምት እስከ ማይጠብሪ ግዳጀን ተወጥቻለሁ፡፡ በጓዶቻችን መስዋእትነት እና በእኛ ጽናት ለሠላም ሥምምነት የበቃችው ሀገር የሰጠችኝን አዲስ አደረጃጀት ተቀብዬ ለማገልገል ቁርጠኛ ነኝ” ነው ያሉት ሀገር በፈለገቻቸው ጊዜ ሁሉ ዝግጁ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት የሕልውና እና የሕግ ማስከበር ግዳጆች ሁሉ ከበላይ ብርጌድ እስከ ጽናት ክፍለ ጦር በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ተሰልፈው ተዋግተው አዋግተዋል የቀድሞው የአማራ ልዩ ኀይል አባል እና የጽናት ክፍለ ጦር አዛዥ የነበሩት ኮሚሽነር ታከለ ኪሮስ፡፡ በሕልውና ዘመቻው የበላይ ብርጌድን እየመሩ በበርካታ አውደ ውጊያዎች አኩሪ ተጋድሎን ከአባላቶቻቸው ጋር የፈጸሙት ኮሚሽነር በላይ ብርጌዷን አሸልሞ የተሸለመ ጀግና አዋጊ እንደኾኑ ይነገርላቸዋል፡፡
“ከወልድያ እስከ ዛታ፤ ከኮረም እስከ አላማጣ በነበሩ አውደ ውጊያዎች የተሰጡኝን ግዳጆች በብቃት እና በላቀ ጀብድ ፈጽሜያለሁ” የሚሉት ኮሚሽነር ታከለ በቀጣይ ሕዝብ እና መንግሥት የሰጧቸውን ኅላፊነት በመቀበል እንደወትሮው ሁሉ ግዳጅን በብቃት ለመወጣት በዝግጅት ላይ እንደኾኑም አስረድተዋል፡፡ እንደየ ወቅቱ እና እንደየ ሁኔታው የተለያየ ግዳጅ መቀበል የወታደር ሥነ-ምግባር ነው የሚሉት ኮሚሽነር ታከለ ሀገር ስትፈልጋቸው ሁሌም ዝግጁ ስለመኾናቸው ነግረውናል፡፡
ሁለቱን ከፍተኛ የቀድሞ አማራ ልዩ ኀይል መኮንኖች የተቀበለው የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽንም መኮንኖቹ የኮሚሽኑን ተልዕኮ እና ተግባራት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የላቀ ድርሻ ይኖራቸዋል ብሏል፡፡
የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ውቤ ወንዴ ወደ ኮሚሽኑ የመጡት የአማራ ልዩ ኀይል መሪዎች በውትድርና ሙያ ለዘመናት የካበተ ልምድ እና ወታደራዊ ዕውቀት ስላላቸው የተሰጣቸውን ኅላፊነት በብቃት ይወጣሉ የሚል ተስፋ አለን ብለዋል፡፡ መኮንኖቹ ምደባ ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ መግባታቸውንም ነግረውናል፡፡
ዘጋቢ:- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!