በፓኪስታን ኢዝላማባድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በይፋ ተመረቀ።

81

ባሕር ዳር: ግንቦት 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በፓኪስታን ኢዝላማባድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በይፋ መመረቁን የኢፌደሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በተለያዩ የትብብር መስኮች ግንኙነታቸውን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያጠናከሩ የመጡት ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን አዳዲስ የግንኙነት ምዕራፎችን እየከፈቱ ይገኛሉ።

ከቀናት በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቀጥታ በረራ ከአዲስ አበባ ወደ ካራቺ የጀመረ ሲሆን በዛሬው ዕለትም በኢዝላማባድ ከአንድ ዓመት በፊት የተከፈተው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዛሬ በይፋ ተመርቋል።

ኤምባሲውን መርቀው የከፈቱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እና የፓኪስታን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ሂና ራቢኒ ካሃን ናቸው።

በኢዝላማድ ተቀማጭ የሆኑ የዳኘሎማሲ ማኅበረሰብ አባላት በተገኙበት የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ የኤምባሲው በይፋ መመረቅ በኢትዮጵያ እና ፓኪስታን ግንኙነት አዳሲ ዲኘሎማሲ ምዕራፍ የከፈተ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን ከሁለትዮሽ ባሻገር በጋራ የሚሠሩባቸው በርካታ ዓለምአቀፍ የጋራ ጉዳዮች እንዳሉ ያስታወሱት አምባሳደር ምስጋኑ፤ የኤምባሲውም መከፈት ግንኙነቱን ለማስፋት እና ለማጠናከር ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልፀዋል።

የተጀመሩ የንግድ፣ የኢንቬስትመንት እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችን እንዲጠናከሩ ኤምባሲው እንደሚሠራ ተነግሯል። ግንኙነቱን አሁን ካለበት ይበልጥ ለማጎልበት የኢትዮጵያ መንግሥት ቁርጠኛ መኾኑንም ተናግረዋል።

የፓኪስታን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ሂና ራቢኒ ካሃን ደግሞ፣ ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን ተመሳሳይ የልማት እና ኢኮኖሚ ፈተና ያለባቸው ሃገሮች መሆናቸውን በመጠቆም ለጋራ ችግር የጋራ መፍትሔን ለመፈለግ ትብብራቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አስታውቀዋል።

አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ እንደመሆኗ የኢትዮጵያ የኤምባሲ በኢዝላማባድ መኖር ከሁለቱ ሀገራት ባሻገር ፓኪስታን ከአፍሪካ ጋር ለሚኖራት ግንኙነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ሚኒስትር ዲኤታዋ ተናግረዋል።

በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ደግሞ፣ ኤምባሲው ከአንድ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በይፋ ለምረቃ እንዲበቃ የፓኪስታን መንግሥት ላዳረገው ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል።

ኤምባሲው ለዘላቂ የሁለቱ ሀገራት ጥቅም መሰረት መሆኑንም አምባሳደር ጀማል አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እ.አ.አ በ1950ዎቹ እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቀድሞው የአማራ ልዩ ኃይል አባላት የክልሉን ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ለመቀላቀል ስልጠና መጀመራቸውን አስታወቁ፡፡
Next articleኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሠራቸው የማነቃቂያ ሥራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።