የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ዛሬ ባደረገው ስብሰባ የኢህአዴግን ውህደት በአብላጫ ድምፅ፣ በስድስት ተቃውሞ አጽድቋል።
በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባው የተነሱ ዐበይት ጉዳዮችን በተመለከተ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ፈቃዱ ተሰማ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በውይይቱም ውህድ ፓርቲው ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝምን እንደሚያስጠብቅ፣ የወሰን እና የማንነት እንዲሁም የራስ አስተዳደር ጉዳይ አሁንም ትኩረት እንደሚሰጣቸው እና ሁሉም ፍትሀዊ ውክልና እንዲያገኙ እንደሚያደርግ ነው በማብራሪያቸው ያስታወቁት።
በውህድ ፓርቲው ብሔራዊ ማንነትን እና ሀገራዊ ማንነትን ባስታረቀ መልኩ ማየት እንደሚገባም ተመላክቷል ብለዋል አቶ ፈቃዱ። አዲስ የሚፈጠረው ውህድ ፓርቲ የቋንቋ ብዝሀነትንም የሚያስተናግድ እንደሆነ ነው ያብራሩት።
በጉዳዩ ላይ ግልጽ ውይይት ከተካሔደ በኋላ ዛሬ ኅዳር 06/2012 ዓ.ም በአብላጫ ድምጽ እና በስድስት ተቃውሞ ጸድቋል ብለዋል አቶ ፈቃዱ።
ውህደቱ የሞግዚት አስተዳድርን እና የእጅ አዙር አገዛዝን በማስቀረት እውነተኛ ፌዴራሊዝምን ለመተግበር እንደሚያስችልም አስገንዝበዋል።
በአስማማው በቀለ