በ5 የፌደራል ተቋማት የተገነቡ የስማርት ኮሚኒኬሽን ክፍሎች እና ሥርዓት ተመርቆ ሥራ ጀመረ።

97

ባሕር ዳር: ግንቦት 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በ5 የፌደራል ተቋማት የተገነቡ የስማርት ኮሚኒኬሽን ክፍሎች እና ሥርዓት ተመርቆ ሥራ ጀመረ። በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተገነቡ ስማርት ክፍሎቹ ዘመኑ ያፈራውን ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙና ለቀላልና ቀልጣፋ የሥራ ግንኙት የሚያግዙ ናቸው።

በየተቋማቱ የተገነቡት ክፍሎቹ ዘመናዊ ስማርት ስክሪን፤ ስማርት ላይቲንግ፤ የተሻሻሉ የቴሌ እና የቪዲዮ ኮንፈረንሶችን ማድረግ የሚያስችሉ ስማርት መሳሪያዎች፣ ምቹ ክፍሎች፤ የአየር ማቀዝቀዣ፤ የድምፅ ብክለትን የሚቀንሱ መሳሪያዎችና የኔትወርክ መሳሪያዎች የተገጠሙላቸው መኾኑን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ የስማርት ኮሙኒኬሽን ክፍሎቹና ፕላትፎርሙ ሥራ መጀመር ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚሰራው ሥራ ውስጥ የራሱን አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለዋል።

በቀጣይ በሁሉም የክልል ፕሬዝዳንት ቢሮዎች እንዲሁም በተመረጡ የፌደራል ተቋማት 20 ስማርት ኮሙኒኬሽን ክፍሎች የመገንባት ሥራ ይቀጥላል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ሥርዓቱ በአካል መገናኘትን በማስቀረት የተቀላጠፈ ስራ ለመሥራት፣ ሥልጠናና ስብሰባዎችን ለማካሄድና ስምሪትን ለመስጠት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

በምዕራፍ አንድ የተገነቡት ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ለገንዘብ ሚኒስቴር፣ በትምህርት ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ትምህርትና ምርምር ኔትዎርክ፣ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ለዲጂታል መታወቂያ እና ለኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን ሲሆኑ በምዕራፍ ሁለት ደግሞ ለ20 ተቋማት ይገነባሉ።

የስማርት ኮሙኒኬሽን ክፍሎቹ በ5ቱም ተቋማት በኦንላይን በተመሳሳይ ሰዓት ተመርቀው ወደ ሥራ ገብተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ የቴክኖሎጂ ትራንስፎርሜሽንን ለማምጣት እየሠራች ነው” በለጠ ሞላ (ዶ.ር)
Next articleየቀድሞው የአማራ ልዩ ኃይል አባላት የክልሉን ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ለመቀላቀል ስልጠና መጀመራቸውን አስታወቁ፡፡