
👉”ጥሩ ውጤት ለማምጣት ተገቢውን ዝግጅት እያደረግን ነው” ተማሪዎች
ባሕር ዳር:ግንቦት 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ወቅቱ ተማሪዎች የድካማቸውን ውጤት ለማየት፣ በጥሩ ውጤትም ወደ ቃጣዩ ደረጃ ለመሸጋገር የሚያስችለውን ፈተና ለመውሰድ የተቃረቡበት ጊዜ ነው። በዚህ ዘገባችን ተማሪዎች በቀጣይ ለሚወስዱት ፈተና ምንያክል ተዘጋጅተዋል ስንል ተማሪዎችን አነጋግረናል። ተማሪዎች ለውጤት የሚያበቃቸውን መንገድ እንዲከተሉም ምክር ከባለሙያ ይዘናል።
የሥነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚመክሩት ፈተና በጉዳዩ ላይ ዕውቀትን ብቻ ሳይኾን ለፈተናው የሚመጥን የሥነ ልቦና ዝግጅትን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። እናም ተፈታኞች ለሚቀርብላቸው ጥያቄ ሁሉ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት በመረጋጋት፣በስክነት፣በአስተውሎት፣ከፍርሃትና መረበሽ በመውጣት የሚያውቁትን፣በትምህርት ቆይታቸው የተረዱትን መሠረት በማድረግ ለውጤት ማብቃት ይኖርባቸዋል።
የሥነ ልቦና ባለሙያው ማስረሻ ታደሰ በባሕር ዳር ከተማ የጣና ሐይቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች ምክርና ድጋፍ ባለሙያ ናቸው።
ባለሙያው እንደሚሉት ተማሪዎች ከአካዳሚያዊ የጥናት ዝግጅት ባልተናነሰ መልኩ የሥነ ልቦና ምልኡነትን መለማመድ፣ እና ማዳበር አለባቸው።
ይኽ ካልኾነ ግን ትምህርቱን በሚገባ ሲከታተል ኖሮ፣በሚገባም አጥንቶ በፈተና ወቅት ያልተረጋጋ፣የሚረበሽ፣የሚጨነቅ ፣አላስፈላጊ ተጠራጣሪነትና የአልችልም ባይነት መጥፎ መንፈስን የተላበሰ ተማሪ ሁሉ የሚያውቀውን ጥያቄ እንኳን በአግባቡ ለመመለስ ይቸገራል ብለዋል ባለሙያው።
ታዲያ ተማሪዎችስ ምን ይላሉ? ለአካዳሚያዊ ውጤታማነት የሚያበቃቸውን የሥነ ልቦና ልምምድ እያደረጉ ይኾን? አስተያየታቸውን የሰጡን ተማሪዎች ምላሽ አላቸው፦
ተማሪ ሀብታሙ ቢሰጥ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነው። ትምህርትን በአግባቡ መከታተል፣ማጥናት እና ካለፉት ልምድ መቅሰም እንደ አንድ ተማሪ የሁልጊዜም ተግባሬ ነው ይለናል። በተለይም በቀጣይ የ12ተኛ ክፍል ሀገር ዓቀፍ ብሔራዊ ፈተናን ለመውሰድ እና የተሻለ ጊዜ ለጥናት በመስጠት፣ የተለየ የሥነ ልቦና ዝግጅት እያደረገ እንደኾነም ነው የነገረን።
ብሔራዊ ፈተናው የተለየ የሚያደርገው አፈታተኑና ለሕይወታችን ወሳኝነቱ ነው እንጂ ከተማርነው፣ እና ከምናውቀው ውጪ አይደለም የሚለው ተማሪ ሀብታሙ የሚያውቁትን ለመመለስ ቀድሞ በሥነ ልቦናም መዘጋጀት ወሳኝነት እንዳለው ግን እረዳለሁ ነው የሚለው።
በተመሳሳይ የ12ኛ ክፍል ተማሪው መስፍን አስፋው በ2015 ዓ.ም ብሔራዊ ፈተና ለመውሰድ የሚያስችል ከንባብ አስከ ሥነ ልቦና ዝግጅት እያደረገ ስለመኾኑ ነው የተናገረው።
“ዘመኑን ለተጠቀመበት ምቹ ዕድሎችን ይዞ የመጣ ነው”የሚለው ተማሪ መስፍን በዕውቀት ራስን ለማበልጸግ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ከትምህርት ቤትና ከመምህራን ባሻገርም ራስን በራስ የማስተማር ዕድሉ ሰፊ ነው ይላል።
የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሊያሻግረው የሚያስችል ዕውቀትን እንዴት መግኘት እንዳለበት፣ያሉትን ዕድሎች የሚረዳ ስጋቶቹን አስቀድሞ የሚያስወግድ የማገናዘብ ዕድሜ ላይ ያለ ነው ይላል ተማሪ መስፍን።
ዋናው ዓላማውን ለማሳካት የሚያደርገው ቁርጠኝነት ነውና በትጋት የሚጠበቀውን ማድረግ እንደሚገባም ነው የተናገረው። “ትምህርት ከታች የሚወድቀው ከላይ ተስፋ ሲጠፋ ነው” የሚለው ተማሪ መስፍን የእኔ ካለፉት በመመማር ለውጤት መብቃት፣ በአርዓያነት ለሚከተሉኝ ታናናሽ እህት ወንድሞቼ ኩራት መኾን አለብኝ ብሎ ማሰብ ይገባል ነው የሚለው።
በቀጣይ ለሚወስደው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናም በቂ ዝግጅት እያደረገ ስለመኾኑ፣ ለጥሩ ውጤት የሚያበቃውን መንገድም እየተከተለ እንደኾነ ነግሮናል።
ሌላኛዋ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ፀደንያ ሙሉቀን በትምህርት ህልምን ለውጤት ለማብቃት የሚያስችላትን ሁሉ እያደረገች ስለመኾኗ ነው የነገረችን።
“በእቅድ አጠናለሁ፣ምክርን፣ልምድን ከመምህራን፣ከቤተሰቦቼን ፣ከጓደኞቼም ጭምር ተጠቅሜ ለብርታት እጠቀምበታለሁ” ብላለች ተማሪ ፀደንያ።
ዛሬ ላይ 11ኛ ክፍል ነኝ ወደ 12ኝ ክፍል የሚያሻግረኝ ፈተናም በጥሩ ውጤት ለማለፍ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረኩ ነው የምትለው ተማሪዋ ለቀጣይ ብሔራዊ ፈተና ውጤታማነት የሚጀምረው ከትላንት፣ከዛሬውና ለነገው ባለኝ ዝግጁነት ነውና ከማንበብ፣ እና ማጥናት ባሻገር አስፈላጊውን የሥነ ልቦና ዝግጅት ሁሉ አደርጋለሁ ብላለች።
የሥነ ልቦና ባለሙያው ማስረሻ ታደሰ እንደሚሉት ጎበዝ ተማሪ አንባቢ ነው፣ጎበዝ ተማሪ ከአስተማሪዎቹ፣ከጓደኞቹ፣ከወላጆቹ እና ልምድ ካላቸው ሁሉ የሚወስደውን ያውቃል፣ለስኬት የሚያደርሰውን መንገድም መርጦ ይጠቀማል።
እናም ተማሪዎች በትምህርታቸው ስኬታማ ለመኾን “በፈተና ወቅት ለስኬት የሚያደርሳቸውን መንገድ መዘንጋት የለባቸውም” ይላሉ ባለሙያው። ሥነ ልቦናችን የምልኡነት 50 በመቶውን የሚወስድ ጉዳይ መኾኑን ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚያስረዱት።
ውጤታማ ተማሪ ማንበብን፣ማጥናትን፣ትምህርቱን ክፍል ውስጥ በአግባቡ የሚከታተል ብቻ ሳይኾን በዕቅድ የሚመራ፣ትጉህ ፣ከሌሎች ልምድ በመቅሰም ምሳሌዎችን ቀምሮ ለውጤት የሚያበቁ መንገዶችን ጠንቅቆ የሚረዳ፣በተግባርም የሚጠቀም ስለመኾኑም ባለሙያው መክረዋል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!