ፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ውጤታማ የማኅበራዊ ሥራዎችን መሥራቱን አስታውቋል።

65

ባሕር ዳር: ግንቦት 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል  በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ውጤታማ የማኅበራዊ ሥራዎችን መሥራቱን አስታውቋል። ፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል የአብረናት እንተግብር ፕሮጄክት  በደቡብ ጎንደር ዞን ለአምስት ዓመታት ሲተገብር የቆዬውን ሥራ የማጠቃለያ ግምገማ አካሂዷል።

በማጠቃለያ ዝግጅቱ  የአማራ ክልል ሴቶች ሕፃናት ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ፣ የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ ይርጋ ሲሳይ፣  የፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል ካንትሪ ዳይሬክተር መንግሥቱ አስናቀ ( ዶ.ር) ተገኝተዋል።

ድርጅቱ በደቡብ ጎንደር ዞን  በአምስት ወረዳዎች እና በደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር በወጣቶች ጤና፣ በሥነ ተዋልዶ እና በሌሎች  ጉዳዮች ሲሠራ ቆይቷል።  እብናት፣ ላይ ጋይንት ፣ ታች ጋይንት፣ ስማዳና ሊቦከምከም ወረዳዎች ደግሞ ፕሮጄክቱ የተተገበረባቸው ወረዳዎች ናቸው።

ወጣቶች የራስ መተማመናቸው እንዲዳብር፣ ለችግሮች መፍትሔ እንዲፈልጉ፣ በሥነ ልቦና ጠንካራ እንዲኾኑ በርካታ ሥራዎችን እንዳከናወነ ተገልጿል።  ድርጅቱ ተከታታይ ስልጠናዎችን በመሥጠት ለውጥ እንዲመጣ ማድረጉንም አስታውቋል።  ልጆች እንዲማሩ፣ ራሳቸውን እንዲያውቁ እና ራዕይ እንዲሰንቁ ልዩ ልዩ ትምህርቶችን እና ስልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷልም ተብሏል። ጥሩ ዜጋ ለመፍጠር የሚያስችል መልካም ሥራዎችን ማከናወኑም ተመላክቷል።

ከላይ ጋይንት የመጡት አቶ ገዳም ዓለሙ ድርጅቱ ሥር ሠዶ የነበረውን ያለ እድሜ ጋብቻ እንዲቀርና  ልጆች እንዲማሩ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።  በኑሮ ላይ ተፅዕኖ ሲያሳድሩ በነበሩ ችግሮች ላይ ጥሩ ለውጥ ማሰየታቸውንም ተናግረዋል። ቀደም ሲል ሴቶች በቤታቸው ውስጥ በገንዘባቸውም  አያዙበትም ነበር፣ ሴት ወደማጀት  ወንድ ወደችሎት የሚባል ጉዳይ ነበር፣  አሁን ያ አስተሳሰብ ተቀርፏል ነው ያሉት።

ከሊቦ ከምከም ወረዳ ይፋግ የመጣችው  ሶፍያ የሱፍ  ፓዝ ፋይንደር በትምህርቷ እንድትበረታ እንዳደረጋት ነው የተናገረችው። የአጭር ጊዜ ግቦችን ማሳካት የረጅም ጊዜ ግቦችን ለማሳካት አስፈላጊ እና ቀዳሚ መኾኑን መንገድ እንደከፈተላትም ተናግራለች። በሥነ ልቦና ጠንካራ እንድትሆን እና የትኛውንም ነገር መሥራት እንደምትችል እንዳስተማራትም ገልጻለች።

በአዕምሯቸው ላይ መልካም ነገር እንደቀረፁባቸውም ተናግራለች። በሥነ ተዋልዶ፣ በንፅህና አጠባበቅ እና በምግብ ዝግጅት ላይም ሰፊ ስልጠና እንደተሰጣቸው ነው የተናገረችው።

የፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል ካክትሪ ዳይሬክተር መንግሥቱ አስናቀ (ዶ.ር) በኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት የሠራ ድርጅት መኾኑን ተናግረዋል። ድርጅቱ ለማኅበረሰብ ጠቃሚ የሆኑ ሥራዎችን መሥራቱን ገልጸዋል።  ድርጅቱ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ለዓመታት ሢሠራ መቆየቱንም ተናግረዋል። በቆይታውም በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጉን ነው የገለጹት።

ድርጅቱ  በጤና ዘርፍ በትኩረት እየሠራ መኾኑን ነው  የተናገሩት። ወጣቶች የገንዘብ አጠቃቀም ላይ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። በተሠራው ሥራ ብዙ ለውጦች መገኘታቸውን ነው የተናገሩት።

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ይርጋ ሲሳይ ድርጅቱ በዞኑ በማኅበራዊ ዘርፉ መልካም ሥራ መሥራቱን ገልጸዋል። ሥራው በዞኑ ቀጣይነት ያለው ሥራ እንዲሠራ መሠረት የጣለ መኾኑንም ተናግረዋል። መንግሥት እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ደርጅቶች በጋራ መሥራት ትውልድን ለመቅረጽ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል። ድርጅቱ በማኅበራዊ ዘርፉ ትኩረት አድርጎ በመሥራቱ ዞኑን ተጠቃሚ አድርጓልም ነው ያሉት።

ሕፃናት ላይ የሠራው ሥራ ታላቅ መኾኑንም ገልጸዋል። ሕፃናት ላይ በመሥራቱ ትምህርታቸውን በትኩረት እንዲማሩና ጤናቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል። ድርጅቱ የጀመረው ሥራ በመንግሥት ሊቀጥል የሚገባው መልካም ልምድ መሆኑንም ገልጸዋል። ለሠሩት ሥራም ምስጋና አቅርበዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”የሌማት ትሩፋት ኢትዮጵያ ዜጎቿን ከመቀንጨር ችግር ለመታደግ እና ከምግብ ጋር በተያያዘ የሚወጣውን  የውጭ ምንዛሬ የሚያስቀር ፕሮጀክት ነው” አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
Next article“ተማሪዎች በፈተና ወቅት ለስኬት የሚያደርሳቸውን መንገድ መዘንጋት የለባቸውም” የሥነልቦና ባለሙያ