”የሌማት ትሩፋት ኢትዮጵያ ዜጎቿን ከመቀንጨር ችግር ለመታደግ እና ከምግብ ጋር በተያያዘ የሚወጣውን  የውጭ ምንዛሬ የሚያስቀር ፕሮጀክት ነው” አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

86

አዲስ አበባ:ግንቦት 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ  ታገሰ ጫፎ የሌማት ትሩፋት ኢትዮጵያ ዜጎቿን ከመቀንጨር ችግር ለመታደግ እና ከምግብ ጋር በተያያዘ የሚወጣውን  የውጭ ምንዛሬ የሚያስቀር ፕሮጀክት ነው ብለዋል ፡፡

“ከቤተ ሙከራ እስከ አዝመራ” በሚል በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረው የግብርና ሳይንስ ኤክስፖ ዛሬም በሳይንስ ሙዚየም ቀጥሏል። በዛሬው ፕሮግራም የሌማት ትሩፋትን በመተግበር የምግብ ዋስትናችንን እናረጋግጣለን በሚል ሀሳብ የፓናል ውይይት እየተካሔደ ነው።

በፓናል ውይይቱ የእንስሳት ሀብት ባለሙያዎች ፣ተመራማሪዎች ፣የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ የዘርፉ ተቋማት ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።

በፓናል ውይይቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ የግብርናን መዋቅራዊ ሽግግር በማምጣት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት እና ለኢንዱስትሪዎች በቂ ግብዓት መስጠት እንዲችል ይሠራል ብለዋል።

አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮችን እያነቃቃ ያለው የሌማት ትሩፋት ፕሮጀክት ከተጀመረ አንስቶ 25 ሚሊዮን የአንድ ቀን ጫጩት ማከፋፈል የተቻለ ሲኾን 102 ሚሊዮን ላም እና ጊደር ማዳቀል መቻሉ ማሳያ መኾኑን ሚኒስትሩ አንስተዋል።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው ከቤተ ሙከራ እስከ አዝመራ በሚል የተከፈተው የግብርና ዓውደ ርዕይ ለግብርና መዘምን ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳለው አንስተዋል። የበጋ ስንዴ እና የሌማት ትሩፋት ግብርናው በኢትዮጵያ እየተነቃቃ እንደኾነ አንስተዋል።

በእንስሳት ሀብት በአፍሪካ ትልቁን ቁጥር የያዘቸው ኢትዮጵያ በዘርፉ መጠቀም አለመጀመሯ  የተመጣጠነ ምግብ ችግር እየዳረጋት እና የሀገሪቱን ህጻናት ለከፍተኛ መቀንጨር እያጋለጠ መኾኑን ተናግረዋል። ይህን ከፍተት ለመሙላት የእንስሳት እና እንስሳት ተዋፅዖ ምርት 25 ሚሊዮን ዶላር ኢትዮጵያ በአንድ ዓመት ብቻ ወጭ ታደርጋለች ብለዋል።

የሥርዓተ ምግብ ችግርን ማስተካከል የውጭ ምንዛሬን በመቅረፍ አርሶ አደሮችን እና ሸማቾቹን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመው የሌማት ትሩፋት ከ2015 ዓ.ም አስከ 2018 ዓ.ም ድረስ በአግባቡ ለመተግበር ሁላችንም መትጋት ይገባናል ብለዋል።

ይህ ፕሮግራም ለኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማማረጋገጥ እንደሚጠቅም ያነሱት ደግሞ የዓለም አቀፉ የእንስሳት ሀብት ምርምር ተቋም(ILRI) የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ናሙኮሎ ቾቪች ናቸው፡፡ እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ  የአየር ንብረት ለውጥ በሚያመጣው ችግር ተጋላጭ የኾነው የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠናን የድርቅ ችግር መቋቋም እንዲቻል ጥቅም ያለው ሲሆን  የህጻናቱን ፍላጎት በማሟላት በአዕምሮ የበለጸጉ ህጻናትን ለማሳደግ የሚጠቅም ፕሮግራም ነው ብለዋል።

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ በቀጣይ 30 ዓመታት የምትመራበትን የዝቅተኛ ካርበን ልቀት ስትራቴጂክ ዕቅድ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ይፋ አደረገ።
Next articleፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ውጤታማ የማኅበራዊ ሥራዎችን መሥራቱን አስታውቋል።