
አዲስ አበባ:ግንቦት 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በስትራቴጂክ ዕቅዱ ሥነሥርዓት ላይ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍፁም አሰፋ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በእጅጉ እየተፈተነች ትገኛለች ብለዋል። የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ድንበር ዘለል ነው ያሉት ሚኒስትሯ ኢትዮጵያና ሌሎች ታዳጊ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚፈጠሩ የድርቅና ጎርፍ እንዲሁም በአንበጣ መንጋ የተነሳ ለምግብ እጥረት፣ ለአየር ወለድ በሽታዎች መስፋፋት፣ ለሥርዓተ ምህዳርና ብዝሀ ህይወት መመናመንና ውድመት ሲዳረጉ ማየት የተለመደ ነው ብለዋል።
መንግሥት አሳሳቢነቱን ተረድቶ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ2013 እስከ 2022 በሚቆየው የአስር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥን ጉዳይ በዋናነት ማካተቱን ዶክተር ፍፁም ገልጸዋል፡፡ ሚኒስትሯ እንዳብራሩት በ2012 ዓ.ም ግምገማ 82 ቢሊዮን ዶላር በመጽሐፍ ሽያጭ በማሰባሰብ ከ200 በላይ ፕሮጀክቶች ተሠርተዋል፡፡ 104 ነጥብ 97 ሚሊዮን ቶን ካርቦንዳይኦክሳይድ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት መቀነስ መቻሉንም ተናግረዋል ።
ዛሬ ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያ የረጂም ጊዜ የአነስተኛ የካርቦን ልቀትና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የልማት ስትራቴጂ ዓላማ እ.ኤ.አ. በ2050 አካባቢ የምንለቀው የሙቀት አማቂ ጋዝ ከምናስወግደው ጋር ተመጣጣኝ (ኔት ዜሮ) እንዲኾን ነው ብለዋል።
በዚህም ከ30 ዓመታት በኋላ ከተለመደው አሠራር ከ66 በመቶ የሀገር ውስጥ ምርት የተሻለ እድገት ማሰመዝገብ እንደሚቻል ተናግረዋል።
በ30 ዓመቱ ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት ስትራቴጂክ ዕቅድ ይፋዊ ማስተዋወቂያ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ የሚከሰት ችግር በሁሉም የልማት ዘርፎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል ብለዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆችን የአኗኗር ዘይቤ በእጅጉ እያዛባ ይገኛል ነው ያሉት አቶ ደመቀ።
ኢትዮጵያም ችግሩን በመረዳት፡-
👉የአረንጓዴ አሻራ ልማት ፕሮግራም፣
👉የውኃ ፍሳሽ አያያዝ እና ንፅህና ፕሮግራም እና
👉የኃይል ልማት ዘርፍና የተቀናጀ የአካባቢ የተፈጥሮ
ሃብት ልማት ፕሮግራሞችን እያከናወነች ትገኛለች በተለይም አረንጓዴ አሻራን አፍሪካዊ ለማድረግም ተምሳሌታዊ ሥራ እየሠራች መሆኗን ጠቁመዋል።
አቶ ደመቀ በኃይል ልማት ዘርፍ ኢትዮጵያ ከውኃ ፣ከነፋስ ፣ ከፀሐይ እና ከጂኦተርማል ታዳሽ ኢነርጂ እምቅ አቅሟን ተጠቅማ እያለማች እንደኾነም አስረድተዋል፡፡ ይፋ የተደረገው ስትራቴጂ የኢትዮጵያ መንግሥት በሚቀጥሉት 30 ዓመታት ለመገንባት ያሰበውን የንፁህ መጠጥ ውኃ እና የአረንጓዴ ልማት ራዕይን የሚያሳይ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል።
በዚህ አጋጣሚ ኢትዮጵያዊያንና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለስኬታማነቱ ተገቢውን ሚና እንዲጫወቱና አብረው እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግስቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!