“በማሣው ላይ የተሠራውን እርከን በፍሬ የሞላው ጀግና አራሽ”

114

ደብረ ማርቆስ: ግንቦት 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን ቢቡኝ ወረዳ እንገኛለን። “ደብረ ሲና አስማረ” በተባለች ቀበሌ ውስጥ። ቀበሌዋ ከደጋማው የቢቡኝ ወረዳ ቀበሌዎች በተለየ ሞቃታማ ናት። ጤፍ እና በቆሎ በስፋት ይመረታል። ማንጎ፣ ብርቱካን እና ቡናም በአርሶ አደሮች ማሣ ላይ ሰልጥኖ ይታያል።

ዓይናችን ወደ ወደደው የማንጎ ጫካ ገባን። የወጣቱ አርሶ አደር ይበልጣል ጌታሁን ማሣ ነው። አርሶ አደር ይበልጣል በ2004 ዓ.ም የአስረኛ ክፍል ትምህርቱን በማለፊያ ውጤት አጠናቅቋል። ትምህርቱን አልቀጠለም።  “ትምህርቴን ማቋረጤ የማይደገፍ ቢኾንም ትቸው ወደ እርሻ ገብቻለሁ” ብሏል ይበልጣል።

ወጣቱ የማሣውን ዳርቻ እና መካከል በማንጎ ቡና እና ብርቱካን ሞልቶታል። በፍሬ የዛለው የማንጎው እና ብርቱካን ተክል ያስቀናል። ማንጎው በቁጥር ከመቶ በላይ ነው። በዚያ ላይ ብርቱካን እና ቡናው በየመካከሉ አለ።

ወጣቱ አርሶ አደር ይህንን ሁሉ የሚያደርገው  ከአባቱ በተሰጠው ጠባብ የእርሻ መሬት ላይ ነው። ጤፍ፣ በቆሎ እና ሌሎችንም ሰብሎች ያመርታል። የአፈሩን ለምነት ለመጠበቅ በማሳው ላይ እርከን ሠርቷል።

ወጣት ይበልጣል “በእርሻ ማሣየ ላይ የተሠራው እርከን አይቦዝንም” ይላል። እውነትም አላቦዘነውም። በጤፍ እና በቆሎ ማሣው ላይ እርከኑን ተከትሎ የተደረደረው  ማንጎ እና ብርቱካን እንኳንስ ፍሬው ጥላውም ያስደስታል።

ወጣቱ ወደ ፍራፍሬ ልማት ከገባ አምስት ዓመት ኾኖታል። ከተከለው የማንጎ እና የብርቱካን ተክል ጥቅም ማግኘት ጀምሯል። “የመጀመሪያው ጥቅም ራሴን እና ቤተሰቦቸን አትክልት እና ፍራፍሬ እንደየፍላጎታችን በመመገብ ጤናማ ቤተሰብ መፍጠሬ ነው” ይላል። ከጓሮ ከተመረተው ሁሉም አይነት ፍራፍሬ  ቅድሚያ ለራሱ እንደሚመገብ አጫውቶናል።

ወጣት ይበልጣል አንድ እግር ማንጎ እስከ 7 መቶ ፍሬ ይይዛል ብሏል። አንድ ፍሬ ማንጎ እስከ 10 ብር እንደሚሸጥም ጠቅሷል። በዚህ ሒሳብ ሲሰላ ወጣቱ ጥሩ ገቢ እንደሚያገኝ ማወቅ ይቻላል።

አሁን ላይ የገጠሩ ቤቱ ሙሉ ነው፣ የእርሻ በሬዎች ባለቤት ነው፣ ወደ ከተማ ዘልቆ ቦታ በመግዛት ቤት እንደሠራም ነግሮናል። የይበልጣል ታታሪነት የሚያስደንቅ ነው። ይህ ሁሉ የሚኾነው “ባልቦዘነው የማሣው ላይ እርከን” መኾኑ

ደግሞ ወጣቱን “ጀግና” ያደርገዋል።  በብዙዎች ማሣ መካከል ቦዝኖ የሚታየውን እርከን ጀግናው አራሽ ግን በፍሬ ሞልቶታና።

በቢቡኝ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የደብረሲና አስማረ ቀበሌ የአትክልትና ፍራፍሬ መስኖ ባለሙያ አቶ ባንተላይ ታምሬ አካባቢው ማንጎ፣ ብርቱካን፣ አቮካዶ እና ሌሎችንም አትክልትና ፍራፍሬዎች ቢያለሙበት ውጤት የሚያስገኝ ስለመኾኑ ተናግረዋል። ወጣት ይበልጣል በዘርፉ ላይ በታታሪነት እየሠራ እንደሚገኝ ባለሙያው ገልጸዋል።

በተክሎች ላይ የሚከሰተውን በሽታ ከወረዳ እና ዞን ጋር በመኾን ለመከላከል በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑም አቶ ባንተላይ ተናግረዋል።

በቀበሌው የሚኖሩ ሌሎች አርሶ አደሮችም ከእርሻ ጎን ለጎን በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት በመሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሙያዊ ድጋፍ እንሰጣለን ብለዋል። በቀበሌው 708 አርሶ አደሮች በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ተሳታፊ እንደኾኑም አቶ ባንተላይ ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለመኸር ምርት ከ8 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሜትር ኩዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቷል” የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ
Next articleኢትዮጵያ በቀጣይ 30 ዓመታት የምትመራበትን የዝቅተኛ ካርበን ልቀት ስትራቴጂክ ዕቅድ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ይፋ አደረገ።