
ደብረ ብርሃን:ግንቦት 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ላለፋት ተከታታይ ዓመታት ካጋጠሙ የሰው ሠራሽ ማዳበሪያዎች እጥረት ትምህርቶችን በመውሰድ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራቱን መምሪያው አስታውቋል::
የመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ ተውልኝ ሽባባው እንደአለፉት ዓመታት ሁሉ ለመጭው የመኸር ወቅትም ዞኑ ሊያዘጋጀው ከሚጠበቀው የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ውስጥ ዘገባው እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 50 ነጥብ 2 በመቶ መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡
ባለሙያው እንደሚሉት ካለፉት ዓመታት ትምህርት በመውሰድ ለ2015/16 የመኸር ምርት 8 ሚሊዮን 186 ሺህ 652 ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀት በመቻሉ እጥረቱን ማቃለል ተችሏል፡፡
ከተዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ውስጥም 1 ሚሊዮን 956 ሺህ 207 ሜትር ኩዩቢ ጥቅም ላይ መዋሉን ነው ያስረዱት፡፡
በዞኑ በመጭው የመኸር ዘመን 498 ሺህ 758 ሄክታር መሬትን በሰብል ለመሸፈንና ከዚህም 17 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
የምርት ዘመኑን በታቀደው መሠረት ለመፈጸም የምርጥ ዘር ዝግጅት፣ የተባይና መጤ አረሞች ቅድመ መከላከል ሥራዎች ከወዲሁ በቅንጅት እየተሠሩ ስለመሆኑም ባለሙያው ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!