“ሚሊዮኖች ጎብኝተውታል፣ ቢሊዮን ብሮች ተገኝቶበታል”

66

ባሕር ዳር: ግንቦት 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ከቱሪዝም ዘርፉ ገቢ መገኘቱን ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡

ድንቁን ምድር ሚሊዮኖች ጎብኝተውታል፣ የገዘፈ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ባሕልና እሴት አይተውበታል፣ ተምረውበታል፡፡ የታሪኩን ግዝፈት፣  የባሕሉን፣ የተፈጥሮውን ውበት ማየት የሚሹ ሁሉ እየፈለጉ ከትመውበታል፣ መልካም ጊዜ አሳልፈውበታል፡፡ ታይቶ የማይጠገበው እና ተዝቆ የማያልቀው ውበቱ ሚሊዮኖች እንዲመጡበትና እንዲሰነባብቱበት አድርጓል፡፡

ተጨርሰው የተጀመሩ ጥበቦች ያሉበት፣ የዓለም ጥበብ ያልደረሰባቸው ድንቅ አብያተ ክርስቲያናት የተቀረጹበት፣  ታሪክ የሚነገርባቸው፣ ሃይማኖት የሚጸናባቸው፣ ኢትዮጵያ የምትገለጽባቸው ገዳማትና አድባራት የበዙበት፣ ጥንታዊ መስጊዶች የሚገኙበት፣  አጀብ የሚያሰኙ አብያተ መንግሥታት የታነጹበት፣ ረጅሙ ወንዝ ግዮን (ዓባይ) የሚመነጭበት፣ ምስጢርና ጥበብን፣ ታሪክና ዕውቀትን፣ መንፈሳዊነትና ጥንታዊነትን እየነገረ የሚፈስስበት፣ ገዳማትና አድባራትን ያቀፈው ጣና የሚገኝበት ድንቅ ምድር፡፡

ከፍታና ታላቅነት፣ ድልና ጀግንነት፣ ነጻነትና አንድነት፣ አትንኩኝ ባይነትና አይደፈሬነት የሚገለጽባቸውና የሚዘከርባቸው  ታሪካዊ ሥፍራዎች የበዙበት፣ የውኃ ማማ የሆኑት ጮቄና ጉና ያሉበት፣ የዓለምን ቀልብ የሚስበው፣ ብርቅ የሆኑ እንስሳትን የሚሰበስበው እና የሚመግበው፣ ውብ የተፈጥሮ ውበት የሚገለጽበት፣ ተፈጥሮን ያደንቅ ዘንድ ሕዝብ ሁሉ የሚሰባሰብበት ታላቁ ራስ ደጀን የሚገኝበት ውብ ምድር፡፡

የሚያስቀኑ ባሕሎች፣ ያልተበረዙና ሀገር ያጸኑ እሴቶች የመሉበት፣  ውበትና ፍቅር የሚገለጽባቸው በዓሎች የሚከበሩበትም ነው የአማራ ክልል፡፡  በቤተ መንግሥቱ ወይም  በቤተ እምነቱ ታሪክን፣ የአመራር ጥበብን፣ የሀገር ፍቅርን፣ የጸና እሴትን መማር  የሚሻ ሁሉ ወደ አማራ ክልል ይመጣል፡፡ ተዝቆ ከማያልቀው የጥበብ ውቅያኖስ፣ የታሪክ ሐይቅ  እንደየአቅሙ እየጠጣ ይመለሳል፡፡ ኑሮዬ ጥበብ ከሚቀዳበት፣ ታሪክ ከሚጠጣበት ጋር ይሁን ያለው ደግሞ በዚሁ ሥፍራ በፍቅር ይኖራል፡፡

የአማራ ክልል ታይተው የማይጠገቡ ድንቅ ሥፍራዎች፣ ውብ ባሕሎች ሞልተውታል፡፡ የሚያጓጉ፣ የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ የከበሩ መስህቦች ያሉበት ክልል ነው፡፡ የመስህብ ሥፍራዎቹ ታሪክን፣ ጀግንነትን፣ ሃይማኖትን፣ እሴትን፣ ተፈጥሮን ሁሉንም ነገር የሚገልጹና የሚዘክሩ ናቸው፡፡

ከዓመት እስከ ዓመት ቢታይ፣ ቢጎበኝ የማይሰለችና የማይጠገብ ድንቅ ምድር ነው፡፡ ክልሉን በርካታ ጎብኚዎች ለመዳረሻነት ይመርጡታል፡፡ በረሃማ ከሆኑ አካባቢዎች እስከ እጅግ ቀዝቃዛ የሆኑ ሥፍራዎችን አጣምሮ የያዘ ሥፍራ ነውና በየትኛውም ጊዜ ይወደዳል፣ ይናፈቃል፡፡

ይህን ድንቅ ምድር ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጎብኚዎች መርጠውታል፡፡ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አበበ እምቢአለ ክልሉን በዘጠኝ ወራት 9 ነጥብ 1 ሚሊዮን  የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ይጎበኙታል ተብሎ እቅድ ተይዞ ከ13 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ጎብኚዎች መጎብኘታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በዘጠኝ ወራት ከእቅድ በላይ የሆነ አፈጻጸም መኖሩንም ገልጸዋል፡፡ በሃይማኖታዊና ባሕላዊ በዓላት ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ ከፍተኛ ሥራዎች በመሠራታቸው የጎብኚዎች ቁጥር ከተጠበቀው በላይ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡

ከወርኃ ነሐሴ ጀምሮ እስከ ጥር መጨረሻ ድረስ ከፍተኛ የሆነ የሀገር ውስጥ ጎብኚ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም መኖሩ ለጎብኚዎች መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡ በዘጠኝ ወሩ 103 ሺህ 138 የውጭ  ሀገር ጎብኚዎች ክልሉን ይጎበኙታል ተብሎ ዕቅድ ተይዞ 21 ሺህ 282 ጎብኚዎች ብቻ መጎብኘታቸውንም ገልጸዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ጥሎት የነበረው ስጋትና ጦርነቱ የፈጠረው ጫና የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ቁጥር እንዲቀንስ ማድረጉንም አስታውቀዋል፡፡ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በስፋት እንዲመጡ ሰፊ ሥራ እንደሚጠይቅም ተናግረዋል፡፡ ዲፕሎማቶች እና አምባሳደሮች ክልሉን እየጎበኙ መሆናቸው የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ፍሰት እንደሚጨምርም ገልጸዋል፡፡

በሀገር ውስጥ ያለው የጎብኚዎች ቁጥር መጨመር አበረታች መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የውጭ ጎብኚዎች የሀገሪቱን ሰላምና የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሠረት በማድረግ የሚጨምር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በክልሉ በዘጠኝ ወሩ ከሀገር ውስጥ ጎብኚዎች  2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ መገኘቱን ነው የገለጹት፡፡ ከውጭ ቱሪስቶች 486 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዶ 75 ሚሊዮን ብር መገኘቱንም ተናግረዋል፡፡ በውጭ ሀገር ጎብኚዎች የሚፈለገውን ማሳካት ሳይቻል መቅረቱንም ነው የነገሩን፡፡

በክልሉ በዘጠኝ ወሩ በአጠቃላይ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዶ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉንም አስታውቀዋል፡፡ በአማራ ክልል ምጣኔ ሃብትን ያሻግራሉ ተብለው ከሚታሰቡ ዘርፎች መካከል አንደኛው ቱሪዝም መሆኑን ያነሱት ኃላፊው የክልሉን ሕዝብ ምጣኔ ሃብት ለመጨመር በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑንምተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ጊዜያት በርካታ ጎብኚዎችን የሚስቡ መዳረሻዎች እንደሚኖሩም አመላክተዋል፡፡ አደጋ የተጋረጠባቸውን ቅርሶችም እየጠገኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ጎብኚዎች ወደ ክልሉ በስፋት እንዲመጡ ለማድረግ እየሠሩ መሆናቸውን የተናገሩት ኀላፊው ሰላም የቱሪዝም የመጀመሪያው ግብዓት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ክልሉ ሰላማዊ ከሆነ የቱሪዝም ፍሰቱ ከዚህ በላይ እንደሚጨምርም አስረድተዋል፡፡

በአማራ ክልል የቱሪዝም ፍሰቱ እንዲጨምርና ኢኮኖሚው እንዲያንሠራራ ሁሉም ለሰላም ትኩረት ሠጥቶ እንዲሠራም ጠይቀዋል፡፡ ሁሉም የሰላም አምባሳደር በመሆን ክልሉ ሰላማዊ መሆኑን ማሳየትና ጎብኚዎችን መሳብ ይጠበቅበታልም ብለዋል፡፡ የሰላም ስጋት መኖር የቱሪዝም ሃብቱን በእጅጉ እንደሚጎዳውም አንስተዋል፡፡

ሰላምን መንግሥትና ሕዝብ ተባብረው ሊጠብቁት ይገባል ነው ያሉት፡፡ ቱሪዝሙ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን ማነቃቃት መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ባለፉት 9 ወራት ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል” የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር
Next article“ለመኸር ምርት ከ8 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሜትር ኩዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቷል” የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ