
ባሕር ዳር: ግንቦት 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራና አፋር ክልሎች በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች በመልሶ ግንባታና ማቋቋም አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። በጤና ሚኒስቴር በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት መልሶ ማቋቋም አስተባባሪ ዶክተር ኤርሚያስ ደጁ እንደገለጹት በአማራና አፋር ክልሎች በመልሶ ማቋቋም ጉዳት የደረሰባቸው የጤና ተቋማት ዳግም ሥራ ጀምረዋል። በዚህም በክልሎቹ ጉዳት የደረሰባቸውን 42 ሆስፒታሎች እና 448 ጤና ጣቢያዎች በመልሶ ግንባታና ማቋቋም ዳግም ሥራ መጀመራቸውን ነው የገለጹት።
ለተቋማቱ ዳግም ሥራ ማስጀመርያ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መድረጉንም ዶክተር ኤርሚያስ ተናግረዋል። በሆስፒታሎቹ ቀደም ሲል ሲሰጡ የነበሩ አገልግሎቶችን በሙሉ አቅም ማከናወን እንዲቻል በቀጣይነትም የተጠናከረ ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን አረጋግጠዋል። በመልሶ ግንባታና የማቋቋሙ ሥራ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ የመንግሥት ሆስፒታሎች የተለያዩ እገዛና ድጋፎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውም ተገልጿል።
የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ኮሌጅ እና የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመልሶ ግንባታ ላይ መሳተፋቸውንና የወደሙ የጤና ተቋማት መደበኛ አገልግሎት እንዲጀምሩ የሚያስችል ሥራ ሲሰሩ መቆየታቸውም መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!