
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ቢሮው የዘጠኝ ወራት እቅዱን 84 በመቶ ማከናወን መቻሉን ነው ለአሚኮ የገለጸው። በክልሉ ሥራና ስልጠና ቢሮ የሥራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ዳይይሬክተር ስላባት ሰዋገኝ ለአሚኮ ኦንላይን ሚዲያ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የሚመዘገበው የሥራ ፈላጊ ቁጥር የሥራ እድል ለመፍጠር ከታሰበው እቅድ በላይ ነው።
በበጀት ዓመቱ ለአንድ ሚለዮን 203 ሺህ 180 ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ቢታቀድም የሥራ ፈላጊው ቁጥር ግን በዘጠኝ ወራት ብቻ ከዓመቱ እቅድ በላይ አንድ ሚሊዮን 234 ሺህ 515 ሥራ ፈላጊ ዜጎች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።
በተያዘው በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ለ867 ሺህ 192 ዜጎች በቋሚና በጊዚያዊነት የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋም እና በቅጥር ዜጎች የሥራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። 41ሺህ 442 ኢንተርፕራይዞች መቋቋማቸውንም አብራርተዋል። 58 ሺህ 960 ዜጎች በቋሚነት የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በተፈጠረው የሥራ እድል 86 በመቶው ወጣቶች ናቸው።
በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት ዘርፍ ለበርካቶች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል የሚሉት አቶ ስላባት የእቅዱን በግብርናው ዘርፍ 32 ነጥብ 6 በመቶ፣ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ደግሞ 46 በመቶ ማከናወን ተችሏል ነው ያሉት።
ባለፉት 9 ወራት በተፈጠረው የሥራ እድል ተጠቃሚዎች፦
👉24 ሺህ 770 የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን፣
👉52 ሺህ 265 የሚኾኑት ደግሞ የቴክኒክና ሙያ ምሩቃን፣
👉3 ሺህ 200 ከስደት ተመላሽ ዜጎችንም የሥራ እድሉ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት አቶ ስላባት።
ለዘርፉ ስኬታማነት ቢሮው በኢንተርፕራይዝ ለሚደራጁ ሥራ ፈላጊዎች እንደየ ሥራ እቅዳቸው የብድር ማመቻቸት፣ የመሥሪያና መሸጫ ሸዶችን ማመቻቸት፣ የሥልጠናና ማማከር አገልግሎት ላይ በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል ዳይሬክተሩ።
በክልሉ በሥራ እድል ፈጠራ ተግባር ላይ የአመለካከት፣ የእውቀትና ክህሎት ጉድለት እና ከመንግስት አቅም በላይ የሥራ ፈላጊው ቁጠር መኖር የዘርፉ ፈተና ኾኗል ተብሏል። ቢሮው ገበያው የሚፈልገውን በእውቀት ፣በክህሎትና በአመለካከት የበቃ የሰው ኃይል ለማፍራት ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደኾነም ተገልጿል።
የሥራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ዳይሬክተሩ ስላባት ሰዋገኝ፤ ወጣቶች በንድፈ ሃሐብ ከሚማሩት ባሻገር፣ ፍላጎታትን መሰረት ባደረገ መልኩ መደራጀት፣ገበያው የሚፈልገውን እውቀት፣ክህሎትና አመለካከት ይዘው መገኘትን መረዳት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል ።
ዘጋቢ፦ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!