“የዲጅታል ነዳጅ ግብይት በመላ ሀገሪቱ ከዛሬ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል” የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር

167

👉በአገልግሎቱ ላይ ችግሮች እንዳያጋጥሙ ዝግጅት ማድረጋቸውን ኢትዮ ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገልጸዋል።
አዲስ አበባ: ግንቦት 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዛሬ የተጀመረው የነዳጅ ግብይትም በዘርፉ የሚያጋጥመውን ማጭበርበር ለማስቀረት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ተብሏል። ነዳጅ በዲጂታል ግብይት እንዲፈጸም የተፈለገው ግብይቱን ለማዘመን እና ማጭበርበርን ለመቀነስ እንደኾነ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተሻለ በልሁ ገልጸዋል። መንግሥት የነዳጅ ድጎማን እየቀነሰ ወደ ቀጥታው ግዥ ለማስገባት እየሠራ ነው። የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ድጎማው ይቀጥላል ብለዋል።እስከ አሁን ናፍጣ 29 ቤንዚን 25 ብር እየተደጎመ መቀጠሉን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

እስከ አሁን ነደጃ በገንዘብ ፣ በካርድ ፣በካሽ እና በኩፖን ግብይት ይካሔድ ነበር ያሉት ሚኒሰትሩ የካሽ ክፍያ ዛሬ የሚያቆም ሲኾን የኩፖን እና የካርድ አገልግሎት የሚጠቀሙት ግን እስከ ሰኔ 30 /2015 ዓ.ም ይቀጥላል ብለዋል።
የነዳጅ ሽያጭ ዛሬ በመላ ሀገሪቱ በድጅታል ተጀምሯል። ይሁን እንጂ በዋናነት የታየው ችግር ተጠቃሚዎች በሚፈለገው ሁኔታ ሳይዘጋጁ መምጣት መኾኑ ተገልጿል። የኢትዮጵያ ነዳጅ እና ኢነርጅ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሒ በበኩላቸው በቁጥር 40 ሚሊዮን የሚኾን ግብይት በዲጅታል ደረጃ ተካሒዷል ብለዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ ኅብረተሰቡ እየለመደው እንደሚሄድ ያሳያል ብለዋል።

በክልሎች ደግሞ 41 ሚሊዮን ብር በኤሌክትሮኒክስ ግብይት መከናወኑን ገልጸዋል። በዚህም የነዳጅ እጥረት ያለባቸው ማደያዎችን ለማወቅ እና ስርጭቱን ለማፋጠን ይረዳል ብለዋል። በአዲስ አበባ ያጋጠመው ከፍተኛ ሰልፍ የተፈጠረው ተጠቃሚዎች የይለፍ ቃላቸውን(ፒን ኮድ ) ረስተው በመምጣታቸው ነው። ይህንን ለመቅረፍ የግንዛቤ እና የውይይት ሥራዎች ተሰርተዋል ብለዋል። እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ በአሁኑ ሰዓትም ዲጅታላይዝ የሚደረገው ነዳጅ ግብይት እና ትራንስፖርት ከሚፈጽሙት ቦቴዎች ላይ መኾኑን አንስተው በአብዛኛዎቹ ቦቴዎች ላይ ጂፒኤስ ተገጥሞላቸዋል። ስለዚህም በነዳጅ ማጓጓዝ ቅሸባ ላይ እናጣለን ብለን የምናስበውን 2 ቢሊዮን ብር ያስቀራል ብለዋል። ማደያ የሌለባቸው ወረዳዎች እና አርሶአደሮች በምን ኹኔታ ግብይት ሊፈጽሙ ነው ለሚለው ጥያቄ ዳይሬክተሯ በቅርብ ከሚገኙ ነዳጅ ማደያዎች ጋር በማስተሳሰር በድጅታል መንገድ መገበያየት እንዳለባቸው መመሪያ ወጥቷል ብለዋል ። በአንድ በኩል ደግሞ ኤጄንቶች ጥሬ ገንዘብን ወደ ድጅታል ገንዘብ ሊቀይሩ የሚችሉብትን መንገድ እንከተላለን ብለዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል መኒ ኀላፊ ብሩክ አድሀና እንዳሉት አንድ ቢሊዮን ብር በላይ የነዳጅ ግብይት በቴሌ ብር ተፈጽሟል ብለዋል። በአካባቢያዊ ቋንቋዎች እና በመገናኛ ብዙኃን ግንዛቤ እያስጨበጥን ነው። ባለሙያችም በማደያዎች በመገኘት ደንበኞች የይለፍ ቃል እንዲያገኙ እየተሰራ ነው ብለዋል። የቴሌ ብር ደንበኞች 31 ሚሊዮን ደርሰዋል ያሉት ኀላፊው 1 ሺህ 100 ማደያዎች በሀገሪቱ ቴሌ ብርን ይጠቀማሉ ብለዋል። ደንበኞች በማንኛውም ማደያ እንዳይቸገሩ በማደያዎች ባለሙያዎች በመመደብ ባንኩ አገልግሎት እየሰጠ መኾኑን የገለጸው ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው። በባንኩ የሲቢኢ ብር ዳይሬክተር መንግስቱ እንዳላማው በሲቢኢ ብር አገልግሎቱን በቀጥታ ማግኘት የሚችልበትን ዕድል ባንኩ አመቻችቷል ብለዋል።

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አጼ ቴዎድሮስ የጀመሩት፣ ልጆቹ ያስቀጠሉት”
Next articleበአማራ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ867ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ እድል ተጠቃሚ መኾናቸውን የክልሉ ሥራና ሥልጠና ቢሮ አስታወቀ።