
ባሕር ዳር: ግንቦት 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) እኒያ ጀግና መሪ ያልታሰበውን አሰቡት፣ ያልታለመውን አለሙት፣ የደከመውን አበረቱት፣ የተለያዬ የመሰለውን አንድ አደረጉት፣ ትናንት ላይ ቆመው ዛሬን አዩት፡፡ ከጊዜያቸው አብዝተው ቀድመዋል፣ ከዘመናቸው ፈጥነዋል፣ ከዘመኑም ልቀዋል፡፡
ሀገራቸውን አብዝተው ወደዷት፣ ስለ ፍቅሯ በበረሃ ተመላለሱላት፣ ጦርና ጎራዴ ከታጠቁ ጋር ያለ ፍርሃት ገጠሙላት፣ ክብሯን ለማስመለስ ከሞት ጋር ተናነቁላት፣ የተወረወረባቸውን ጦር እያነሱ፣ የጎራዴውን ፍላጻ በክንዳቸው እየመለሱ በጀግንነት ተፋለሙላት፣ ረፍት ሳይሹ ተንከራተቱላት፣ በቤተ መንግሥት መቀመጥ ሳያሻቸው፣ ዘውድና ካባውን ለብሰው፣ በሰረገላ ላይ ተቀምጠው፣ በቀኝ በግራቸው፣ በፊት በኋላቸው በመኳንንቱና በመሳፍንቱ ተከበው፣ በአማረው በአባቶቻቸው ቤተ መንግሥት መኖር ሳያምራቸው፣ ስለ እርሷ ኳተኑላት፣ እንቅልፍ ትተው ተብሰለሰሉላት፣ ስለ ፍቅሯ ሁሉ ነገራቸውን ሰጧት፡፡
ከዘመኑ አልቆ የታያቸው ሕልም አላስተኛ አላቸው፣ እውን ሆኖ ያዩት ዘንድ ይሻሉና አንከራተታቸው፣ በሞት ፍላጻ ውስጥ አስጓዛቸው፣ የሀገራቸው ተስፋ አሻግሮ እየታያቸው፣ የሀገራቸው ስልጣኔ ድቅን እያለባቸው አጓጓቸው፡፡ በአንድ ጀንበር አንድ አድርገዋት፣ በአንድ ጀንበር ከስልጣኔ ላይ ስልጣኔ ደራርበውላት ቢያዩዋት ምኞታቸው ነበር፡፡ ዳሩ ሩቅ የሆነ ሕልማቸው ብዙ ጊዜ ያስፈልገው ነበር፡፡ ጊዜም ብቻ አልነበረም፤ ሕልማቸውን የሚነግሩት፣ ራዕያቸውን የሚያጋሩት ሰውም ያስፈልጋቸው ነበር፡፡
ራዕያቸው እውን ይሆን ዘንድ የደከመውን ዙፋን አስቀድመው አበረቱት፣ እንደ አባቶቻቸው ሁሉ አስፈሪ ግርማን አላበሱት፣ በየመንደሩ ሆኖ ከእኔ በላይ ወንድ ከየት አለ የሚለውን አደብ አስገዙት፣ ጎራ የለየውን ሁሉ በአንድ አስፈሪ ዙፋን ሥር አሰባሰቡት፣ በአንዲት ሠንደቅ አንድ አደረጉት፡፡ አንድነት ራዕያቸውን እውን ለማድረግ፣ ታላቅ ሀገርን ለመምራት ታላቁ ምርጫ ነበርና፣ መረጡት፡፡
ከዘመን የቀደሙት፣ ከትውልዳቸው በራዕይ የተለዩት፣ በሀገራቸው ፍቅር የታሰሩት፣ ስለ ሀገራቸው የኖሩት፣ ስለ ሀገራቸው ያላቸውን ሁሉ የሰጡት፣ ነብሳቸውን ጭምር ለሀገራቸው ክብርና ፍቅር ያበረከቱት ጀግናው ንጉሥ ታላቁን ሥራ ጀመሩት፡፡ ሀገራቸው ታላቅ የምትሆንበትን፣ ከጠላቶቿ የምትጠበቅበትን ቴክኖሎጅ በሀገራቸው ምድር አስጀመሩ፡፡ ለዓመታት ሕልም ሆኖ አላስተኛ ያላቸውን ራዕይ በጋፋት ምድር እውን ይሆን ዘንድ ሞከሩት፡፡ አዕምሯቸው ላይ የነበረውን ራዕይ በተግባር አዩት ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ፡፡
ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ጥበብን አብዝተው ይፈልጓት፣ ስልጣኔን አብዝተው ይከተሏት ነበርና ባሕር አቋርጦ ወደ ሀገራቸው የገባውን ሰው ሁሉ “ ምን ሥራ ታውቃለህ?” እያሉ ይጠይቁት ነበር ይባላል፡፡ ሥራ አውቃለሁ ያላቸው የተገኘ እንደሆነ ደስታቸው ከፍ ይላል፡፡ ራዕያቸው እውን የሆነ እየመሰላቸው አምላካቸውን ያመሰግናሉ፣ ተስፋም ያደርጋሉ፡፡ ምንም አላውቅም የሚል ባጋጠማቸው ጊዜ ደግሞ አብዝተው ይከፋሉ፡፡ ዕውቀትና ስልጣኔን የሚከታተሉ ሩቅ አዳሪ ናቸውና ጥሩ የሚሠራ ሰው ፍለጋ ሁልጊዜም ይጠይቃሉ፡፡
በዘመናቸው ወደ ሀገራቸው የገቡ የውጭ ሀገር ሰዎችን ሰባስበው፣ ራዕያቸውን ነግረው፣ ሕልማቸውን አዋይተው እውን ያደርጉላቸው ዘንድ አደረጉ፡፡ ቴዎድሮስ በጋፋት ምድር ራዕይ ተገበሩባት፣ ያልተቋጨ ሕልም አኖሩባት፣ ቃል ኪዳንም አስቀመጡባት፣ ታላቅ አደራም አኖሩባት፣ ለልጅ የሚሆን አደራ አተሙባት፡፡ ቴዎድሮስ በአንድ በኩል ሀገራቸውን አንድ እያደረጉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሀገራቸው በስልጣኔ ከፍ እንድትል ይታትሩ ነበር፡፡ ዳሩ ከዘመናቸው የቀደመው ሕልማቸውን፣ አላስተኛ አላስቀምጥ ያላቸውን ራዕያቸውን በሚፈልጉት ልክ ሳይፈጽሙት፣ የሀገራቸውን ታላቅነት በራዕያቸው ደረጃ ሳያዩት ዘመን ቀደማቸው፡፡ ሕልማቸውና መንፈሳቸው ግን ዛሬ ያለውን ትውልድም ይገዛል፣ ራዕያቸው በልጅ ልጆቻቸው ላይ ይኖራል፡፡
አጼ ቴዎድሮስ ያስጀመሩትን ድንቅ ስልጣኔ፣ ልጆቹ እያስቀጠሉት ነው፡፡ ከቴዎድሮስ ራዕይ ላይ ራዕይ የወሰደው፣ የቴዎድሮስን ሕልም እውን ለማድረግ ሥንቅ የሰነቀው የደብረ ታቦር ዪኒቨርሲቲ የጋፋትን ስልጣኔ እየቀሰቀሰው ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በአጭር ጊዜና በራስ አቅም ሮኬቶችን የማስወንጨፍ ሥራ ሠርቷል፡፡ ሮኬት ማስወንጨፉ የቴዎድሮስን ሕልም የማስቀጠልና ኢትዮጵያን ዘመኑ ከደረሰበት ስልጣኔ የማድረስ ዓላማ ያለው ነው፡፡ በደብረ ታቦር ዪኒቨርሲቲ የጋፋት የሕዋ ምህንድስና ልማት ማዕከል መስራችና ሰብሳቢ በለጠ ጌታቸው የቴዎድሮስን ጥያቄ ለመመለስ፣ የጋፋትን ዕውቀት ለማሰስ እየሠሩ መሆናቸውን ነግረውኛል፡፡ ማዕከሉ የትናንት ዕውቀትን በመቀስቀስ ሀገርን ታላቅ የማድረግ ዓላማ ሠንቋል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ያስወነጨፈው ሮኬት ከአሁን ቀደም ከተወጨፈው በብዙ መልኩ የተሻለ መሆኑን ነግረውኛል፡፡ ጉዟችን ረጅም በመሆኑ የሚሞከሩት ሮኬቶችም ርቀታቸው ከበፊቱ የረዘሙ ናቸው ያሉት ሰብሳቢው በማዕከሉ የሚሠራው ሥራም ታላቅ ሕልምን ያነገበ ነው ብለውኛል፡፡ ሳተላይትን በሕዋ ላይ የማስቀመጥ ግብ ሰንቀው እየሠሩ መሆናቸውንም ነግረውኛል፡፡ ጋፋት ላይ ተጀምሮ የነበረውን የዕውቀት ጥያቄ በልዩ ልዩ ዘርፍ የመመለስ እና የማሳካት ሕልም ሰንቀዋል፡፡
ጋፋት ላይ የነበረውን ጥያቄ ለመመለስ የተጀመረው ሙከራ ጥሩ መሆኑንም ነግረውኛል፡፡ በጥቂት አቅምና በአጭር ጊዜ እየተሠራ ያለው ሥራ አስደናቂ ነው፡፡ በሰለጠነው ዘመን የሳይንስ እና የዕውቀት የበላይነት ትልቁን ድርሻ ይይዛል፣ ሀገራት የዕውቀት ውጤቱን ይሸጣሉ፣ ቴክኖሎጅው የተሠራበትን ነገር ግን መስጠት አይፈልጉም፣ የሉዓላዊነት ጉዳይ በመሆኑ ይህን ዕውቀት በራስ አቅም መሥራት ታላቅ ነገር ነው ብለውኛል፡፡ ማዕከላቸው ዕውቀትን የመፈለግ ሥራ እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ዓለም ላይ እየተወሰዱ ያሉ የበላይነቶች በዕውቀት ነው፡፡ የቴዎድሮስን ራዕይ እየቀሰቀሰው ያለው ሥራ በሚፈለገው ልክ ድጋፍ እየተደረገለት አለመሆኑንም ነግረውኛል፡፡ ድጋፉ ብቻ ሳይሆን ትኩረቱም አናሳ ነው፡፡ ማዕከሉ ግን ራዕዩን ለመኖር እየሠራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ የቀደሙትን ቆሞ ከማየት መከተል እንደሚሻም ተናግረዋል፡፡
በርካታ ሀገራት የቀደመ ዕውቀታቸውን ነው የቀሰቀሱት፣ ኢትዮጵያም የቀደመውን ዕውቀት የመቀስቀስ ዕድል ከፊቷ አለ፣ ኢትዮጵያ የቀደሙ ድንቅ ዕውቀቶች እና ጥበቦች አሏት፣ የቀደሙትን ጥበቦች ከቀሰቀሰች ከሚፈለገው ሥፍራ ትደርሳለች፡፡ በማዕከሉ ውስጥ የሚሠራው ሥራ ግሩም በመሆኑ አጼ ቴዎድሮስ ይቻላል እንዳሉ ሁሉ የይቻላል መንፈስ አድጓል ነው ያሉት፡፡ ለሁሉም ነገር የሚቀድመው ሥነ ልቦና ነው ያሉት ሰብሳቢው አባቶች ሁሉንም ማሸነፍ እንደሚቻል አሳይተውናል፣ ሥነ ልቦናቸው የሚቀዳው ከአባቶች አሸናፊነት ነው፣ ትውልዱም ከአሸናፊነት የሚቀዳውን ሥነ ልቡና በመያዝ ለአሸናፊነት መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡ የአባቶቼ ልጅ ነኝ ለማለት የአባቶችን ሥራ መሥራትና ራዕያቸውን ማስቀጠል ግድ እንደሚልም ገልጸዋል፡፡
ተክለጻድቅ መኩሪያ ስለ አጼ ቴዎድሮስ ሕልም ሲገልጹ “ አጼ ቴዎድሮስ በጠቅላላው የንጉሥነት ሕይወታቸው ቢገመገም ሰፊ ምኞት ያላቸው ሆነው ይገኛሉ” ብለዋቸዋል፡፡ እርሳቸው ከልጅነታቸው እስከ መጨረሻዋ ስንብታቸው ድረስ ለሀገራቸው ኀያልነት ሕልም፣ ጥልቅ ፍቅር ነበራቸው፡፡ ያን ሕልምና ጥልቅ ፍቅር ጨርሰው ሳይኖሩት፣ በጅምር ትተውት፣ ለልጅ ልጅ ሰጥተውት አለፉ፡፡ ዓመታት አልፈው፣ ዘመናት ተሻግረው ልጆቻቸው የአባታቸው ራዕይ የታያቸው፣ የአባታቸው ሕልም ከእንቅልፍ የቀሰቀሳቸው፣ ከአባታቸው ባሻገር ያለች ጮራ የታየቻቸው ይመስላል፡፡ ያቺን መልካም ራዕይ አብዝተው ከወደዷትና በጽናት ከተከተሏት ይደርሱባታል፡፡ በኀያልነትም ይመላለሱበታል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!