
ባሕር ዳር: ግንቦት 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመርና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ አስተዋጽዖ ያላቸው ሁለት ረቂቅ ዓዋጆችን አጽድቋል።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 17ኛ መደበኛ ስብሰባው ከግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረቡለትን የሁለት ረቂቅ ዓዋጆች ሪፖርትና የውሳኔ ኃሳብ መርምሮ አጽድቋል።
ስለ ዕጽዋት ዘር ለመደንገግ ማሻሻያ የተደረገበትን ረቂቅ ዓዋጅና የግብርና አምራችና አስመራች ግንኙነትን ለመወሰን አዲስ የወጣ ዓዋጅን ነው ምክር ቤቱ ያጸደቀው።
ዓዋጆቹ በግብዓት አቅርቦት፣ በተጠቃሚነት፣ ምርታማነትን በማሳደግ በዘርፉ የሚስተዋሉ የአሰራር ክፍተቶችን በመሙላት ለግብርና ምርትና ምርታማነት የራሳቸውን አስተዋጽዖ እንደሚያደርጉ ተገልጿል።
የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ የረቂቅ ዓዋጆቹን ይዘት፣ ከአስፈላጊነትና ማስተካከያ የተደረገባቸው እንዲሁም አዲስ የተጨመሩ አንቀጽና ድንጋጌዎችን ለምክር ቤቱ አብራርተዋል።
ስለ ዕጽዋት ዘር ለመደንገግ ማሻሻያ የተደረገበት ረቂቅ ዓዋጅ ለግብርና ማቀነባባሪያ ኢንዱስትሪዎች የጥሬ ዕቃ አቅርቦትን ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የነበረውን የሕግ ክፍተት ለመሙላት የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
ዓዋጁ የነበሩ ክፍተቶችን በመሙላት የግሉን ዘርፍ በሚያበረታታና የዘር ኢንዱስትሪን ለመገንባት ትልቅ ሚና በሚኖረው መልኩ ማሻሻያ ተደርጎበታል ነው ያሉት።
በተጨማሪም ለተጠቃሚዎች ጥራቱ የተረጋገጠ ምርጥ ዘር በአይነት፣ በመጠንና በወቅቱ ለማቅረብ እንዲያግዝ ዓዋጁ ማሻሻያ ተደርጎበታል ብለዋል።
የግብርና አምራችና አስመራች ግንኙነትን ለመወሰን አዲስ የወጣ ዓዋጅ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶና አርብቶ አደሮችን ጥቅም ያስከብራል ሲሉ አብራርተዋል።
በአምራችና አስመራች መካከል ፍትሃዊና ጤናማ ግንኙነትን የሚፈጥር፣ ለአፈጻጸም አስቸጋሪ የነበሩ አሰራሮችን ለማስተካከል ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
አርሶና አርብቶ አደሩን ከአስተማማኝ ገዥዎች ጋር በማገናኘት ጠንካራ የገበያ ትስስር የሚፈጥሩና ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ ግብዓቶችን አስመራቹ ተደራሽ በማድረግ የመንግሥትን ጫና ለመቀነስ በዓዋጁ ተደንግጓል።
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት የሚያስችልና ለማምረት የሚያበረታታ ዓዋጅ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የግል ባለሃብቶች በግብርና ዘርና ማዳበሪያ ምርት እንዲሰማሩ ዕድል በመፍጠር የግብርና ግብዓት አቅርቦት ችግርን ከመፍታት አንጻር ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
በዓዋጁ የተቀመጡ መብትና ግዴታዎችን እንዲሁም አጠቃላይ የዓዋጁ ይዘት ላይ ለአርሶ አደሩና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም ረቂቅ ዓዋጆቹ የሚያስገኙትን ጠቀሜታ ከግምት በማስገባት ሁለቱንም ዓዋጆች በሙሉ ድምጽ አጽድቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!