
ባሕር ዳር: ግንቦት 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን 650 ሺህ ሄክታር የሚታረስ መሬት አለ። ከዚህ ውስጥ ከ156 ሺህ ሄክታር በላይ የሚኾነው መሬት በአሲዳማነት የተጠቃ በመኾኑ ምርታማነቱ እንደቀነሰ የዞኑ ግብርና መምሪያ መረጃ ያመላክታል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ፈንታሁን ቸኮል የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ችግር ውስጥ የገባውን የአፈር ጤንነት በመመለስ ምርታማነቱን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። “የአፈር ጤንነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየታወከ ነው” ያሉት አቶ ፈንታሁን ይህንን ለማከም ከሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ወጥቶ የተፈጥሮ ማዳበሪያን የመጠቀም ልምድ መዳበር እንዳለበት ተናግረዋል።
መምሪያ ኀላፊው የተፈጥሮ ማዳበሪያን ማዘጋጀት እየገጠመ ያለውን የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ እጥረት እና የዋጋ መናር ችግር ለመፍታት ብቻ ታልሞ መኾን የለበትም ብለዋል። የአርሶ አደሮች የኑሮ መሠረት የኾነውን አፈር ህልውና መጠበቅ ከሁሉም ተግባር ቅድሚያ ተሰጥቶት መዘጋጀት አለበት ሲሉም ገልጸዋል። ስለዚህም “የተፈጥሮ ማዳበሪያን መጠቀም አማራጭ ሳይኾን ግዴታም ኾኗል” ሲሉ አቶ ፈንታሁን ተናግረዋል።
እንደዞን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት በትኩረት እየተሠራበት ስለመኾኑም ገልጸዋል። ለ2015/2016 የምርት ዘመን የሚኾን 10 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ታቅዶ ነበር ብለዋል። በተፈጠረው ንቅናቄ አሁን ላይ ከ12 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።
አቶ ፈንታሁን አርሶ አደሮች ያዘጋጁትን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ወይም ኮምፖስት በአግባቡ ለመጠቀም የግንዛቤ ክፍተት አልፍ አልፎ እንደሚገጥም ገልጸዋል።አርሶ አደሮች ከዘር ቀደም ብለው በመሬታቸው ላይ በመበተን ውጤታማ እንዲኾኑ በባለሙያ እየተደገፉ ስለመኾኑም አቶ ፈንታሁን ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!