
ባሕር ዳር: ግንቦት 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ፕላን ኢንተርናሽናል፣ የአማራ ክልል ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት እና የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በጋራ ዓለም አቀፍ የሴቶች የአይ ሲ ቲ ቀንን እያከበሩ ነው።
የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ሴቶችን የቴክኖሎጅ ዕውቀት እንዲኖራቸው ለማድረግ ቢሮው እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። በከተማ ተማሪዎች በኮምፒውተር ታግዘው እንዲማሩ፣ በገጠር የሚማሩ ተማሪዎች ደግሞ ዕውቀቱን በሬዲዮ ተደራሽ ማድረግ መጀመሩን ተናግረዋል።
ሴቶች ተወዳዳሪ እና የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነቶች በአግባቡ እንዲወጡ ራሳቸውን በቴክኖሎጅ ማብቃት እንደሚጠበቅባቸውም ወይዘሮ ብርቱካን አስረድተዋል።
በዓሉ በዚህ መልኩ መከበሩ ልምድ ለማግኘት እና አዳዲስ ሀሳቦችን ለማግኘት እንደሚረዳም አስታውሰዋል።
ወይዘሮ ብርቱካን በቴክኖሎጅ አማካኝነት በክልሉ ተስፋፍቶ የሚታየውን የልጅነት ጋብቻ እና ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል መታቀዱንም ተናግረዋል።
ከአንዳሳ አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጣችው የስድስተኛ ክፍል ተማሪዋ የሽመቤት ወርቁ በትምህርት ቤቷ እየተሠጠ የሚገኘው የአይሲቲ ስልጠና ትምህርቷን በአግባቡ እንድትከታተል እና ውጤት እንድታመጣ አስችሏታል። በተለይ እንግሊዝኛ ትምህርት በአግባቡ እንድትከታተል እና አዳዲስ ዕውቀት እንድታገኝ እንደረዳት አንስታለች።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ኢንጅነሪንግ እና ሒሳብ ኢንኩቤተር ሴንተር የ11ኛ ክፍል ተማሪ የኾነችው ዮስቲና አበራ በኮዲንግ ስኪል ተማሪዎች የማኅበረሰቡን ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እንዲሠሩ እየተደረገ መኾኑን ተናግራለች።
ተማሪ ዮስቲና ከጓደኞቿ ጋር በመተባበርም ማየት የተሳናቸው ሰዎች እንዲያነቡ፣ ሰዎችን እንዲለዩ እና መኪና መንገድ ለማቋረጥ የሚያግዝ ቴክኖሎጅ መሥራታቸውን ተናግራለች። ዮስቲና ሁሉም ሰው ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም የሥራ ጫናውን ማቅለል አለበትም ብላለች። ባለሃብቶች የተሠሩ ቴክኖሎጅዎችን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ የሚኾኑበትን መንገድ ቢያመቻቹ ሥትልም ጠይቃለች።
ፕላን ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር መቅድም ጉልላት “ዲጅታል ዕውቀት” ለሁሉም በሚል መሪ መልዕክት ዓለም አቀፍ የሴቶችን የአይሲቲ ቀን እያከበሩ መኾኑን ተናግረዋል። ወይዘሮ መቅድም በዓሉን ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር ማክበር የተፈለገው በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በሳይንስ፣ቴክኖሎጂ፣ ኢንጅነሪንግ እና ሒሳብ እየተማሩ ያሉ ተማሪዎችን ተደራሽ ለማድረግ እና ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ታሳቢ ያደረገ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እና የማኅበረሰቡን የኑሮ ዘይቤ ለማቃለል ሴቶች በአይሲቲ ዘርፍ እንዲሳተፉ ቤተሰብ ትልቁን ድርሻ ሊወስድ እንደሚገባም ወይዘሮ መቅድም አሳስበዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ 66 በመቶ የአይሲቲ ተጠቃሚዎች አሉ። ከዚህ ውስጥ 69 በመቶ ወንዶች ሲኾኑ የሴቶች ድርሻ 31 በመቶ መኾኑ በጥናት መረጋገጡ በበዓሉ ላይ ተገልጿል።
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!