“ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ደርጅቶች ኢትዮጵያ በየቀኑ የምትቀበላቸውን የሱዳን ፍልሰተኞች ሊደግፉ ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

139

ባሕር ዳር: ግንቦት 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ የሚገኙ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅት አስተባባሪዎች ከአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡

ርእሰ መሥተዳድሩ በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ያነጋገሯቸው የተመድ፣ የዓለም እርሻ ድርጅት፣ የዓለም ምግብ ድርጅት፣ ዩ ኤስ ኤ አይ ዲ እና ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ተወካዮች ክልሉ በጦርነት የተጎዳውን አካባቢ መልሶ ለመገንባት እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡

ላለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት ያስከተለው ጉዳት እና ችግሩ የተፈታበት የሠላም አማራጭ ለጎረቤት ሀገራትም ተሞክሮ የሚሆን ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከተፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ ለመውጣት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሠላም ሥምምነት ተከትሎ የአማራ ክልል ሕዝብ እና መንግሥት ለሠላም ያላቸውን ቁርጠኛ አቋም በሚያረጋግጥ መልኩ ለተፈጻሚነቱ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመገንባት ከሚደረገው ርብርብ ጎን ለጎን የተደረሰው የሠላም ሥምምነት ተፈጻሚ እንዲሆን በቁርጠኝነት እየሠራን ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ የፌዴራል መንግሥት እና የክልሉን ጥረት በማገዝ በኩል ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ሚናቸው የላቀ ነው ብለዋል፡፡

የሠላም ሥምምነቱ ዘላቂ እንዲሆን፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እና የተጎዱ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተጠግነው ወደ ሥራ እንዲገቡ ያልተቋረጠ ድጋፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ከሳምንታት በፊት በተፈጠረው የሱዳን የእርስ በእርስ ግጭት ምክንያት በአማራ ክልል በኩል በየቀኑ በርካታ ዓለም አቀፍ ፍልሰተኞች እየገቡ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል የፍልሰተኞችን ደኅንነት ከመጠበቅ ባለፈ የሰብዓዊ ቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገም ነው ብለዋል፡፡

እስካሁን ባለው ሂደት በርካታ ቁጥር ያላቸው ፍልሰተኞችን በክልሉ በኩል ኢትዮጵያ እየተቀበለች ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ “ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ደርጅቶች ኢትዮጵያ በየቀኑ የምትቀበላቸውን የሱዳን ፍልሰተኞች ሊደግፉ ይገባል” ብለዋል፡፡ በሱዳን የተፈጠረው የርስ በእርስ ጦርነት ከጎረቤት ሀገር ኢትዮጵያ በመማር ሠላማዊ በኾነ መንገድ ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ አቅርቦት አስተባባሪ ካትሪን ሱዚ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ በሱዳን የተፈጠረውን የእርስ በእርስ ጦርነት ተከትሎ በየቀኑ ድንበር አቋርጠው የሚገቡ ፍልሰተኞችን የምትቀበልበት መንገድ የሚመሰገን ነው ብለዋል፡፡ የሱዳን አዋሳኝ የኾነው የአማራ ክልል ሕዝብ እና መንግሥት ፍልሰተኞችን የሚቀበሉበት እና የሚያስተናግዱበት መንገድ ታላቅ አድናቆት የሚቸረው እንደኾነም አስረድተዋል፡፡

በየቀኑ የሚገቡት ፍልሰተኞች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ጫና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይገነዘባል የሚል እምነት እንዳላቸውም የገለጹት አስተባባሪዋ ዶክተር ሱዚ የሕክምና፣ የምግብ እና ሌሎች አፋጣኝ የሰብዓዊ ቁሳቁስ ለማቅረብ እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡ አስተባባሪዋ የአማራ ክልል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሠላም ሥምምነት ተፈጻሚ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኛ አቋምም አድንቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞች አካባቢያዊነትን፣ ሀገራዊነትን እና ዓለም አቀፋዊነትን አጣጥመው መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ” ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
Next articleሴቶች ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዲፈቱ እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።