“እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞች አካባቢያዊነትን፣ ሀገራዊነትን እና ዓለም አቀፋዊነትን አጣጥመው መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ” ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

84

ባሕር ዳር: ግንቦት 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “አዲስ አበባን በአዲስ የዲፕሎማሲ ከፍታ” በሚል መሪ መልእክት የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።

የዓለማችን 3ኛ የዲፕሎማሲ ከተማ የሆነችውን አዲስ አበባ በሁለንተናዊ መልኩ ያላትን ከፍታና ጥቅም በመዳሰስ የዲፕሎማሲ ከፍታነቷ እንዲዘልቅ ለማድረግ ያለመ ውይይት መኾኑን የኢዜአ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ ተናግረዋል።

የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተወካይ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን በመድረኩ አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረትና የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ የበርካታ ሚሲዮኖችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ ናት፤ የአፍሪካውያን መዲና እንድትኾን ብዙ መሥዋእትነቶች በየጊዜው ተከፍለዋል ብለዋል።

ለኢምባሲዎች በነፃ መሬት ከመሥጠት ጀምሮ ጥረቶች ተደርገዋል ያሉት ተወካዩ ከተማዋ ለኢትዮጵያውያንም ሁሉ ምቹ ከተማ እንድትኾን ሊሠራ እንደሚገባ ተናግረዋል። ሕዝቡ በሠላም የሚኖርባት ከተማ እንድትኾን መሠራት አለበትም ነው ያሉት።

በየጊዜው ዘመኑን የዋጁ ማሻሻያዎች ካልተደረጉ የዲፕሎማሲ ተመራጭነቷ ላይቀጥል እንደሚችልም አስረድተዋል። ስለዚህም ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ ሊሠራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

አምባሳደሩ የማኅበራዊና የኢኮኖሚ ልማት ሥራዎች በቅድሚያ ለከተማዋ ነዋሪዎች ያላቸው ፋይዳ ሊገመገም እንደሚገባም አሰረድተዋል፡፡ በፀጥታ ፣ በቴክኖሎጂ ፣ በኢኮቱሪዝምና በሌሎችም መሥኮች የዲፕሎማሲ ከተማዋ አዲስ አበባ ክብሯን አስጠብቃ መሄድ እንደሚገባትም ተናግረዋል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩላቸው እንደ አዲስ አበባ ያለ ከተማ በርካታ የውጭ ሀገራት ዜጎች የሚኖሩበት በመኾኑ አፍሪካውያን መቀመጫችን የሚሏት ከተማ ምቹ መኾን አለባት ብለዋል።

በተለይ አዲስ አበባ አካባቢያዊነት ፣ሀገራዊነትና ዓለማቀፋዊነትን አጣጥመው ሊሠሩና ሊጓዙ ይገባል ያሉት ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ሆቴሎች እና ሁሉም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዓለማቀፋዊነትን ሊላበሱ ይገባል ነው ያሉት። የሚቀረፁ ፖሊሲዎችም ከዚህ አንፃር የተቃኙ መኾን እንዳለባቸውም አብራርተዋል።

“በንፅህና፣ በፀጥታና በሌሎች መገለጫዎች ተመራጭና ምቹ የኾኑ ከተሞች እንዲኖሩን በአርበኝነትና በዓለማቀፋዊ ስሜት መሥራት ይኖርብናል“ብለዋል።

በፓናል ውይይቱ የተለያዩ የመነሻ ጹሑፎች ቀርበው ውይይት እየተካሄደም ይገኛል።

በመድረኩም የባሕርዳርና የሸገር ከተማ ከንቲባዎችን ጨምሮ የተለያዩ የሥራ ኀላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግስቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጥቅም ላይ ሳይውል እየጠፋ የሚገኘው የእጽዋት ዝርያ።
Next article“ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ደርጅቶች ኢትዮጵያ በየቀኑ የምትቀበላቸውን የሱዳን ፍልሰተኞች ሊደግፉ ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)