በበጀት እጥረት ወደ ልምምድ አለመግባታቸውን የላስታ ላልይበላ እግር ኳስ ቡድን ምክትል አምበል ተናገረ።

159

ባሕር ዳር፡ ሕዳር 06/2012 ዓ/ም (አብመድ) ቡድኑ ያጋጠመውን ችገር ለመፍታትም የአካባቢው ማኅበረሰብ ድጋፍ መድረግ እንደሚገባው የቡድኑ አሰልጠኝ ባየ ተፈሪ ጠይቀዋል።

ሌሎች ቡድኖች ለውድድር የሚያበቃቸውን ዝግጅት እያደረጉ ባሉበት ወቅት የላስታ ላልይበላ እግር ኳስ ቡድን ባጋጠው የበጀት እጥረት እስካሁን ተጫዋቾችን ማሰባሰብ እንዳልቻለ የቡድኑ ምክትል አምበል ጸዳሉ አበባው ተናግሯል።

ቡድኑ በ2011ዓ.ም ከሌሎች አቻ ቡድኖች ባነሰ ክፍያ ውጤታማ እንደሆነ የገለጸው ምክትል አምበሉ በበጀት እጥረት እስካሁን ለውድድር የሚያበቃቸውን ልምምድ አለመጀመራቸው ለስፖርቱ ዘርፍ ትኩረት እንዳልተሰጠው ማሳያ እንደሆነ ተናግሯል።

‹‹ቡድኑ ከውጤታማነት ባለፈ የሥራ ዕድል ፈጥሯል፤ ከቅርሱ በተጨማሪ ለከተማው ገፅታ ግንባታ አስተዋፅኦ እያደረገም ነው። ይሁን እንጂ የላልይበላ ከተማ አስተዳደር እና የላስታ ወረዳ በጀት ባለመመደባቸው ቡድኑ ችግር ገጥሞታል›› ብሏል ምክትል አምበሉ ለአብመድ በሰጠው አስተያዬት። ከአካባቢው ባለፈ የሀገር ገፅታ ግንባታ ላይ ከፍተኛ ሥራ እየሠራ ያለን ቡድን ሁለቱ ወረዳዎች ያሏቸውን መልካም ፀጋዎች ተጠቅመው ቡድኑን ሊታደጉት እንደሚገባም አሳስቧል።

በቡድኖች መካከል በሚደረገው የደርሶ መልስ ጨዋታም የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እያደረገ የሚገኝ ቡድን መሆኑን ባለሀብቱ በመረዳት ለማጠናከር ድጋፍ ማድረግ አንደሚገባ ጠይቋል።

የቡድኑ አሰልጣኝ ባየ ተፈሪ ደግሞ ‹‹በብሔራዊ ሊግ ታሪክ ወደ ከፍተኛ ሊግ ለመግባት በተደረገው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት አንደኛ ደረጃን በመያዝ ያለፈ ጠንካራ ቡድን ነው። ቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ከፍተኛ ሊግ ለመግባት ዝዋይ ላይ በተደረገው ውድድር ተሳትፎ በቀጣይ ለሚደረገው ውድድር ልምድ አግኝቷል፣ የተሻሉ ተጫዋቾችም ለተሻሉ ቡድኖች ተመርጠውበታል›› ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ቡድኑን በበጀት እና በትጥቅ ማጠናከር ሲገባ ሁለቱ ወረዳዎች በጀት ባለመመደባቸው ምክንያት እስካሁን ተጫዋቾቹን ማሰባሰብ እንዳልቻሉ አሰልጣኙ ገልፀዋል።

የላል ይበላ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ አቶ ሙሉጌታ ወልደ ሚካኤ ‹‹የከተማ አስተዳደሩ የበጀት እጥረት ስላጋጠመው ቡድኑን ለመደገፍ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል›› ብለዋል።

ቡድኑ በላስታ ወረዳ እና በላልይበላ ከተማ አስተዳደር የጋራ ባለቤትነት የሚተዳደር እንደመሆኑ እስካሁን የላስታ ወረዳ ድጋፉ ዝቅተኛ በመሆኑ ከከተማ አስተዳድሩ አቅም በላይ መሆኑን ነው አቶ ሙሉጌታ የተናገሩት። ይሁን እንጂ የላስታ ወረዳ ድጋፍ የሚያደርግ ከሆነ ከተማ አስተዳድሩ በጀት አፈላልጎ የድርሻውን እንደሚደግፍም ከንቲባው ገልፀዋል።

በወቅቱ የላስታ ወረዳ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ወንድምነው ወዳጅ እንደገለጹት ደግሞ ቡድኑ እንደተመሠረተ አንዲመዘገብ እና አንዳንድ የትጥቅ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ የወረዳው ድጋፍ ዝቅተኛ ነበር። ችግሩንም ለመፍታት የወረዳው የሥራ ኃላፊዎች የደመወዛቸውን 50 በመቶ አዋጥተው 100 ሺህ ብር ለቡድኑ እንዲውል አንደተወሰኑ አስታውሰዋል።

ቡድኑ ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖረው በወረዳው የሚንቀሳቀሱ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን፣ ባለሀብቶችን፣ ማኅበረሰቡንና የመንግሥት ሠራተኞችን ለማሳተፍ እየተሠራ እንደሆነም ነው አቶ ወንድም ነው የገለጹት። ቡድኑ ሰኞ ዝግጅት እንደሚጀምርም ተገልጧል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሰራ

Previous articleለአማራ ሕዝብ ሠላምና አንድነት ሁሉም የየድርሻውን እንዲወጣ የአዲስ ክፍለ ከተማ የአማራ ተወላጆች አሳሰቡ፡፡
Next articleልዩ ልዩ መሣሪያዎችን በመጠቀም ሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን ሲያትሙ የነበሩ የውጪ ሀገር ዜጎችን በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡