
ባሕር ዳር: ግንቦት 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከሰሃራ በታች በሚገኙ በርካታ ሀገራት እንደሚገኝ ይታመናል። በጣም ጠንካራና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ ከኾኑ የእጽዋት አይነቶች ይመደባል። “አፍሪካን ብላክ ውድ” እየተባለም ይጠራል፤ የዞቢ ዛፍ።
ዛፉ በምዕራብ ጎንደር ዞን በሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮች በስፋት ይገኛል። ከፓርኮች ውጭ ባሉ አካባቢዎች በእርሻ ምክንያት እየተመናመነም ይገኛል።
በጎደቤ ብሔራዊ ፓርክ በብዛት ከሚገኙ የእጽዋት ዝርያዎች ውስጥ የዞቢ ዛፍ አንዱ ነው። ዛፉ ብዙም ለእርሻ አገልግሎት በማይውል መሬት ላይ ሊበቅል የሚችል ዛፍ እንደኾነ የጎደቤ ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት የሥነ ምሕዳር ክትትልና ቁጥጥር ቡድን መሪ ይርጋ ታከለ ነግረውናል።
ዛፉ በሀገራችን ከአጥር፣ ከቤት መሥሪያና ከማገዶ ያለፈ አገልግሎት ሲሰጥ አይታይም። ይሁን እንጅ ሱዳንን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ዛፉን ለጥይት ባሩድ፣ ለጦር መሳሪያ ሰደፍ፣ ለጌጣጌጥ፣ ለስኒ፣ በተለይ ደግሞ ለሙዚቃ መጫወቻ መሳሪያነት ሲገለገሉበት ይስተዋላል። ለባሕላዊ መድሐኒትነትና ለቤት ግንባታም አስተዋጽኦው ከፍተኛ መኾኑን ነው ቡድን መሪ የገለጹት።
ግለሰቦቹ እጽዋቱን በመጨፍጨፍ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሱዳን በማጓጓዝ አንድ ዞቢን ከ1 ሺህ 500 ብር በላይ እየሸጡትም ይገኛሉ።
ከሁለት አስር ዓመት በፊት ሴኔጋል እና ጋና የመሳሰሉ ከፍተኛ የዞቢ ዛፍ ያላቸው ሀገራት ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ ከአንድ ሜትር ኩብ 10 ሺህ 900 ዶላር ያገኙ እንደነበር ለአብነት አንስተዋል።
የጎደቤ ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መሠረት ብርሃኑ የዞቢ ዛፍ በሕገወጥ መንገድ ወደ ሱዳን ሲጓጓዝ እንደነበር አንስተዋል። ጽሕፈት ቤቱም ባለፉት ሁለት ዓመታት በሠራው ሥራ በግመልና ትራክተር ወደ ሱዳን ሲወጣ የነበረውን ዛፍ መግታቱን ገልጸዋል።
ዛፉን ሲያጓጉዙ በተገኙ ግለሰቦች ላይም በገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ መደረጉንም አስረድተዋል። የዞቢ ዛፍን ሲያጓጉዝ የተገኘ ግለሰብ ከ5 ዓመት እስከ 12 ዓመት በገንዘብ ደግሞ ከ50 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!