
ባሕር ዳር: ግንቦት 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከሁለት ዓመታት በላይ በዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተጎዳውን የአማራ ክልል መልሶ ግንባታ ሂደት ላይ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች እያደረጉት ባለው እና ማድረግ በሚገባቸው ድጋፍ ዙሪያ ተወያይተዋል።
ጦርነቱ በአማራ ክልል ሕዝብ ላይ ያደረሰው ጉዳት ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ እና ሥነ ልቦናዊ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የተፈጠረውን ችግር ለመቀልበስ የሚያስችል ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል። በክልሉ ላይ የደረሰው ጉዳት መጠነ ሰፊ እንደኾነ ያነሱት ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ለመልሶ ግንባታው ራሱን የቻለ ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል።
እስካሁን ባለው የመልሶ ግንባታ ሂደት ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ያደረጉት ድጋፍ ከደረሰው ጉዳት አንጻር በቂ ነው ባይባልም ለነበረው ቁርጠኛ አቋም በክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት ስም አመስግነዋል። ጉዳቱ ከክልሉ እና ከፌደራል መንግሥት በተጨማሪ የአጋዥ ድርጅቶችን ያልተቋረጠ ድጋፍ ይጠይቃል ብለዋል። በመልሶ ግንባታ ሂደቱ የዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች ድጋፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በተመድ የሪዚዲያንት እና ሂውማኒቴሪያን ኮርድኔተር ዶክተር ካትሪን ሱዚ ጦርነቱ በክልሉ ላይ ያደረሰው ጉዳት ሰፊ መኾኑን ገልጸው ተመድ እና አጋር ድርጅቶች የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ ብለዋል።
እስካሁን ባለው የድጋፍ ሂደት የክልሉ መንግሥት ትብብር የላቀ እንደነበር አንስተው በቀጣይም አብረን ልንሠራ ይገባል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!