
ባሕር ዳር : ሚያዝያ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ካለፈው ዓመት ጀምሮ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ከወትሮው በተለየ መልኩ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሰጠት ተጀምሯል፡፡ በአማራ ክልል የ2015 ዓ.ም ብሔራዊ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ለመውሰድ ከ215 ሺህ በላይ ተማሪዎች ምዝገባ አድርገዋል ነው የተባለው፡፡
የ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ምዝገባ ከመጋቢት 20/2015 ዓ.ም እስከ ሚያዚያ 15/2015 ዓ.ም ድረስ ተካሂዷል፡፡ የተፈታኞች ምዝገባ በትምሕርት ቤቶች በበይነ መረብ ብቻ እንደተካሄደ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የፈተናና ምዘና ቡድን መሪ አቶ ዝጋለ ማሩ በተለይም ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ውስጥ 579 2ኛ ደረጃ ትምሕርት ቤቶች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን የተማሪዎች ምዝገባ ያካሄዳሉ ተብሎ ታቅዶ ነበር ያሉት አቶ ዝጋለ 575 ትምህርት ቤቶች ምዝገባውን ማድረግ ችለዋል ነው ያሉት፡፡ ሰሜን ጎንደር እና ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሚገኙ አራት ትምህርት ቤቶች በአካባቢው ከተፈጠረው ጦርነት ጋር በተያያዘ የተማሪዎች ምዝገባ ማድረግ አልቻሉም ብለዋል፡፡
በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ለመውሰድ 215 ሺህ 760 ተማሪዎች ፈተናውን ለመውሰድ ተመዝግበዋል ያሉት ቡድን መሪው ከዕቅዱ አንጻር አፈጻጸሙ 95 በመቶ ነው ብለዋል፡፡ ምዝገባው በበይነ መረብ ብቻ የሚካሄድ መኾኑ የኢንተርኔት መቆራረጥ እና መሰል ችግሮች አጋጥመው ነበር ብለዋል ቡድን መሪው፡፡
የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየተወሰዱ ካሉ የመፍትሔ አማራጮች መካከል የፈተና ሥርዓቱን ችግሮች ማረም እና ማስተካከል ነው ያሉት አቶ ዝጋለ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሰጠ ያለው የ12ኛ ክፍል ፈተና ችግሮችን በማረም ይቀጥላል ብለዋል፡፡ ፈተናውን በታቀደለት አግባብ ለመስጠት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ተብሏል፡፡
የ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በመጭው ሐምሌ እንደሚሰጥ ትምህርት ሚንስቴር አስታውቋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!