የአውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ስትራቴጂክ አጋርነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሻገር እየሠራ መሆኑን ገለጸ።

81

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ስትራቴጂክ አጋርነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር እየሠራ መሆኑን አስታወቀ።

ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እያከናወነች ላለው ተግባር ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጿል።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ኅብረቱ  ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር እያከናወነ ያለውን ተግባር አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸውና ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጎልበት ስትራቴጂክ ስምምነት በማድረግ እየሠሩ እንደሚገኙም አምባሳደር ሮላንድ ገልጸዋል።

27ቱ የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሚያዝያ 16/2015 ዓ.ም በሕብረቱ የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት ሊቀ-መንበርነት ባደረጉት ስብሰባ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር አዲስ መሰረታዊ መደምደሚያዎችን በሙሉ ድምጽ ማጽደቃቸውን አስታውሰዋል።

ይህ ውሳኔ በአውሮፓ ኅብረትና በኢትዮጵያ መካከል ባለው አጋርነት ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባሕር ለአውሮፓ ቁልፍ ስትራቴጂካዊ አጋር ናት ያሉት አምባሳደሩ የአውሮፓ ኅብረት ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አመልክተዋል።

ይህም ኅብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የአውሮፓ ኅብረት በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ስትራቴጂክ አጋርነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማምጣት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በሰላም ስምምነቱ መሰረት እየተደረገ ያለው ሰብአዊ ድጋፍና ሌሎች ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውንና በሽግግር ፍትሕ መሰረት ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የአውሮፓ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም በማምጣት የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለመፍጠር የተጀመረውን ጥረት እንደሚደግፍም ነው አምባሳደሩ ያመለከቱት።

ኅብረቱ በኢትዮጵያ መደበኛ የረዥም አመት የልማት መርሐ-ግብሩን እንደገና ለመጀመር ዝግጁ እንደሆነም ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኽምጠ ዊከ ጋዜጣ መዜ 30/2015 ዓ.ስ
Next articleከ215 ሺህ በላይ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ለብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና መመዝገባቸውን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡